የአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካና የኢትዮጵያ የባህር በር አማራጮች

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ "የአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካና የኢትዮጵያ የባህር በር አማራጮች" በሚል ርዕስ የፓናል ዉይይት አካሄደ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ሀገራችን ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛቷ ከአፍሪካ 2ኛ ከዓለም 10ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ስትሆን በቀጥታ የባህር በር ከሌላቸዉ ሃገራት በህዝብ ብዛቷ ትልቅ ሀገር መሆኗን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷም ፈጣን እድገት እያሳዩ ካሉት አገራት መካከል እንደምትጠቀስ አዉስቸዉ የነበሯት ወደቦች ከተወሰዱ በኃላ የገቢ ምርት ለማስገባትና የዉጪ ምርት ለማስወጣት የጅቡቲ ወደብን ለመጠቀም ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ወጪ እንዳለባት ገልፀዋል።

ወደብ አለመኖሩ የቢሮክራሲ አሰራር፣ የጊዜ አጠቃቀም መንጓተት፣ የገቢ ምርት ወጪዎችን እንዲንሩ፣ የግብርና ምርቶች የመበላሸት ዕድልን ከፍ በማድረግ፣ ወደብን ለመጠቀም በጎረቤት ሀገር ተፅዕኖ ስር መዉደቅን፣ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳጣ እና በሌሎች ሀገሮች ኢኮኖሚ ስር መዉደቅን እንደሚያስከትል ዶ/ር አያኖ ገልፀዉ በአንፃሩ የባህር በር መኖር የዉጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ፣ የስራ ዕድልን በማሳደግ፣ የገቢና ወጪ ንግድን ለመጨመርና ዕድገትን ለማፋጠን እንዲሁም በቀጠናዉ ተፅዕኖ ፈጣሪ የመሆን አቅምን ከፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል:: ፕሬዚደንቱ ይህን ያህል ትልቅ ሃገራዊ አጀንዳ በሆነው የባህር በር ጥያቄ ፈር ለማስያዝ ምሁራዊ ዉይይት ማድረግ ተገቢ ነዉ ብለዋል።

በፓናል ዉይይቱ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ጉዳዮች ተ/ዲን እና የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ዶ/ር ንጉስ በላይ "የኢትዮጵያ የባህር በር ታሪካዊ ዳራ" ምን እንደሚመስል: ኢትዮጵያ ባህር በር አልባ የሆነችባቸዉ ምክንያቶችንና የባህር በር አስፈላጊነትን በሰፊው የዳሰሰ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ሌላው የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ አቶ አወል መሐመድ "የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዎችና ቀጠናዊ ፍላጎቶች" ምን እንደሆኑ: የአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታን፣ የአፍሪካ ቀንድ ላይ ያለውን የሃያላን ፉክክር፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ዕድልና ተግዳሮቶችን የተመለከተ የዳሰሳ ፅሁፍ አቅርበዋል:: በዚህም የኢትዮጵያ የባህር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ፣ ቀጠናዊ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ተፅዕኖዋን ለማሳደግ የሚደረግ ስትራቴጂካዊ ግዴታ መሆኑን ጠቅሰዋል። አቶ አወል አክለዉም የባህር በር ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ ሰነድ ማዘጋጀት፣ ጥያቄዉን ግልፅ ማድረግ እና ጉዳዩን የህዝብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዉ አማራጭ መንገዶችን መጠቀም ማለትም ሁሉ አቀፍ ድርድርና ዲፕሎማሲ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ ድርጅቶችን መጠቀም፣ የኃይል ምንጭ ሽያጭን እንደመደራደሪያ ማቅረብን፣ የሚዲያና ምሁራን ሚና፣ አለም አቀፍ ድጋፍን ማግኘት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መፍጠር፣ ቀጠናዊ ትስስር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

ሶስተኛው የውይይት መነሻ ፅሁፍ አቅራቢ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ በፍቃዱ ዲሪባ "የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ትክክለኛነት ከአለም አቀፍ ህግ አንፃር እንዴት ይታያል?" የሚለዉን በመድረኩ ያቀረቡ ሲሆን በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አብዱ መሐመድ መድረኩን መርተዋል:: ዶ/ር አብዱ እንደተናገሩት ትናንት የባህር በር በበርበራ ለመጠቀም የስምምነት ሰነድ ተፈራርመን ያገኘነዉን ተስፋ በአስመራም እንደምንደግመዉ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

ፅሁፎቹ ከቀረቡ በኃላም ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በቀረቡት ላይም ከአቅራቢዎቹ ምላሾች ተሰጥቶባቸዉና ዶ/ር አብዱ ማጠቃልያ ሰጥተዉ ዉይይቱ ተጠናቋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et