የሲዳማ ብሔራዊ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪዎች የእድገት

የሲዳማ ብሔራዊ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪዎች የእድገት ፕሮጀክት ጥናት የግምገማ መድረክ ተካሄደ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጋር በትብብር የሰራው የአምራች ኢንዱስትሪዎች የእድገት ፕሮጀክት ጥናት የግምገማ መድረክ በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዷል።

በግምገማ መድረኩ ላይ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ፣ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጲያ ልማት ባንክ፣ ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ሌሎች አምራች ተቋማት የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ ባራሶ መድረኩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው መሰረታዊ ተልዕኮዎቹ በሆኑት የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች በውጤታማነት እየሰራ እንደሚገኝ እና ሲዳማ አዲስ ክልል ሆኖ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ከተለያዩ ቢሮዎች ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም የኢንዱስትሪው ሴክተር ለሀገር እድገት ሚናው የጎላ በመሆኑ በዚሁ ዘርፍ ክልሉ በርካታ እድሎችና እምቅ አቅም እንዳለው በመገንዘብ ይህንን እንዴት መጠቀም ይቻላል የሚለውን መንገድ ለመምረጥ በቀድሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ጥያቄ መነሻነት ዩኒቨርሲቲው ጥናት ማስጠናቱን ጠቁመዋል:: ዶ/ር አያኖ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ሲገልፁ ዓመቱን ሙሉ ልምላሜ የማይርቀው የሲዳማ ክልል ከሰብል ምርት: ፍራፍሬ: አትክልት: ማር: ዶሮ እና የእንስሳት ውጤቶች በተጨማሪ ለውጭ ገበያ የሚውሉ እንደቡና ያሉትን ከማምረት ባለፈ ኢኮኖሚው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥሩን መሸከም እንዲችል ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ማትኮር ግድ እንደሚል አንስተዋል::

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በበኩላቸው ሀገር በቀል ኢኮኖሚን ለማሳደግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የትኩረት አቅጣጫ ተብለው ከተለዩ ዘርፎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪው አንዱ በመሆኑ ቢሮው ለዚሁ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በተጨማሪም የኢንደስትሪ ዘርፉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት፣ ተወዳዳሪ ምርት አምርቶ ወደ ውጭ በመላክ ገቢ ማስገኘት፣ የስራ እድልን መፍጠር እንዲሁም የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ኃላፊነቶችን ይዞ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተጀመረውን "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ለማስፈጸም እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የምርምር እና ጥናት ተቋማት የሆኑት ዩኒቨርስቲዎች በመንግሥት ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች መካከል ሊኖር የሚገባውን ጠንካራ ግንኙነት በጥናት ለይተው በማቅረብ የተሻለ ስራ እንዲሰራ እያደረጉ ያሉትን ተግባር እንዲቀጥሉም አቶ ጎሳዬ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር እና የጥናት ቡድኑ መሪ የሆኑት ዶ/ር ኢ/ር ፋሲካ ቤተ አስር አባላት ያሉት የጥናት ቡድን ተዋቅሮ በክልሉ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ እንቅፋቶችን ለመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ለአንድ አመት የቆየ ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል። በጥናቱ ከተለዩ ግኝቶች መካከልም የኢንዱስትሪዎች በአንድ አካባቢ መከማቸትና በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ብቻ መሳተፍ፣ ባለሀብቶች ደፍረው ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ ማበረታቻዎችና አመቺ ፖሊሲዎች አለመኖር፣ የመሰረተ ልማቶች አለመሟላት እና ጠንካራ የገበያ ትስስር አለመኖር እንደ እንቅፋት መለየታቸውን ተናግረዋል። በመጨረሻም ከተለዩ ችግሮች በመነሳት ኢንዱስትሪዎች በክልሉ ያሉ ሀብቶችን መሰረት አድርገው የሚመሰረቱበት ሁኔታ መመቻቸት፣ በቂ የጥሬ እቃ አቅርቦት፣ የአመራሩ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የገበያ ተደራሽነት ላይ ሊሰራ ይገባል የሚሉ ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውን የጥናት ቡድኑ መሪ ገልጸዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et