የ2016 የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ2016 ስራ ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ።

በዛሬው ዕለት በግብርና ኮሌጅ ገረመው ኃይሌ አዳራሽ በተካሄደው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻፀም ግምገማ ላይ ከወትሮው በተለየ መልኩ ሁሉም የትምህርት ክፍል እና ትምህርት ቤት ኃላፊዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በኘሮግራሙ መክፈቻ ላይ ሲናገሩ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ካሉ አንጋፋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ እንደመሆኑ በድጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ የመማር ማስተማር : ምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር እንዲሁም የማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ላይ መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል። በዚህም ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዕውቅና እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት ኘረዚደንቱ የውስጥ አቅምና አከባቢያዊ ተነጻፃሪ ብልጫና ዕድሎችን መሠረት ያደረገ ጥራት ተኮር የመማር ማስተማርና የምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ግዜ የተሰጠው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ላይ ለተመዘገበው በጣም ጥሩ ውጤት በታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ላይ የሚገኙት ትምህርት ክፍሎች ከተማሪ ጋር ባላቸው ቀጥተኛ ግንኙነትና ተሳትፎ እውቅና እንደሚገባቸው ጠቁመው በዚህ መድረክ ላይ እንዲሳተፉ የተደረገውም በሥራቸው ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመወጣት እና የተሻለ ውጤታማ ሥራ ለመስራት እንዲችሉ ጥያቄዎቻቸውን በቀጥታ በመድረኩ ላይ እንዲያነሱ ታስቦ መሆኑን ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል::

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍስሃ ጌታቸው ባቀረቡት ሪፖርት በ2015 ዩኒቨርሲቲው ለሀገር አቀፍ መውጫ ፈተና ካስቀመጣቸው 2493 ተማሪዎች መካከል በመደበኛው ፕሮግራም 89 በመቶ ያህሉ ማለፋቸውን ገልፀው ውጤቱ እንደ ሀገር በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ከተመዘገበው አማካይ 62.37% አንፃር በጣም የተሻለ ቢሆንም በተለይም በተከታታይ ትምህርት ዘርፉ ላይ በቀጣይ ጠንክሮ መስራትን የሚጠይቅ መሆኑን አብራርተዋል። ምክትል ፕሬዚደንቱ በመውጫ ፈተና ውጤት ዙሪያ በዩኒቨርሲቲው ስር በሚገኙ 8 ኮሌጆች እና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እያንዳንዱ ት/ክፊል ያስመዘገበውን ውጤት በአኃዛዊ ንፅፅር በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ጉዳዩ ከትምህርት ጥራት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ ከአመራር እስከ እያንዳንዱ መምህር ራሱን የሚፈትሽበት ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል።

በማስከተልም በ2016 በጀት ዓመት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በመማር ማስተማር: በምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ መጠነ ሰፊ ስራዎች በዩኒቨርሲቲው ፕላንና ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክተር በአቶ ሙሉጌታ ቡርቃ አማካይነት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

በመጨረሻም በመውጫ ፈተና ውጤት እና በትምህርት ጥራት አተገባበር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ኮሌጆችና የትምህርት ክፍሎች የማበረታቻ ዋንጫና የዕውቅና ሰርቲፊኬት በየደረጃው ተበርክቶላቸው በቀጣይ ሊተኮርባቸው በሚገቡ ነጥቦች ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት አቅጣጫ በመስጠት ኘሮግራሙ ተጠናቋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et