የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል::
ቦርዱ ከተወያየባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ ሲሆን በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጉዳይ እና በመምህራን የፕሮፌሰርነት ደረጃ ዕድገት ጉዳዮች ላይ በሰፊው ተነጋግሮ ውሳኔ ሰጥቷል::
በዚህም መሰረት ዶ/ር አያኖ በራሶ ሁላ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ሆነው እንዲቀጥሉ የተወሰነ ሲሆን ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ ዲራ ደግሞ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚደንት ሆነው እንዲያገለግሉ ተወስኗል::
በተጨማሪም ለአራት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት የደረጃ ዕድገት በየደረጃው ተገምግሞ በዩኒቨርሲቲው ሴኔት የፀደቀውን ውጤት ቦርዱ በዝርዝር ከመረመረ በኃላ ጥያቄውን አፅድቋል:: በዛሬው ዕለት ሙሉ ፕሮፌሰር የሆኑት ከወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ፕሮፌሰር መሰለ ነጋሽ በ"Forest Ecology and Agroforestry" ከማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፊጮ በ"TEFL" እና ፕሮፌሰር መብራቱ ሙላቱ በ"TEFL": እንዲሁም ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ፕሮፌሰር ጀመረ በቀለ በ"Veterinary Parasitology" ናቸው:: ዝርዝሩን በሌላ ዜና እንመለስበታለን::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ለፕሬዚደንቱ ዶ/ር አያኖ በራሶ እና ለአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዚደንቱ ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ በተሰጣችሁ ኃላፊነት እንኳን ደስ አላችሁ እያለ መልካም የስራና የስኬት ዘመን እንዲሆንላችሁ ከልብ ይመኛል::
ሙሉ ፕሮፌሰር ለሆናችሁ የዩንቨርሲቲያችን ምሁራን ደግሞ ለዚህ ውጤት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ እያልን ለሀገራችሁ የበለጠ ምሁራዊ አስተዋፅኦ እንድታደርጉ አደራ እንላለን!