የበይነ መረብ ትምህርት (e-learning) ስልጠና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ።
የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከ e-learning for Strengthening Higher Education (e-SHE) Initiative" ጋር በመተባበር ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ተወካዮች በበይነመረብ ትምህርት (e-learning) ላይ ስልጠና መስጠት ጀመሯል::
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ e-learning ግብረ-ሃይል አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ባዩ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደገለፁት ስልጠናው ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጥራቱን የጠበቀና ተደራሽ የሆነ የመማር ማስተማር ስርዓትን ለመዘርጋት የታለመ ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሰባቱም ግቢዎች የሚማሩ የተማሪዎች ህብረት ተወካይ ተማሪዎች የሚሳተፉበት መሆኑን ነው:: አስተባባሪው መርሃግብሩ ከስልጠናው በተጨማሪ ለሌሎች ተማሪዎችም የማስተዋወቅ ስራን የሚያካትት መሆኑን ገልፀው እንደ ዩኒቨርሲቲም እስከ ዓመቱ መጨረሻ ይሄንን የበይነመረብ ትምህርት አጠቃቀም ስልጠና ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ለማድረስ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡
የe-SHE Initiative አስተባበሪ አቶ ሙሉነህ አጥናፉ በበኩላቸው ስልጠናውን ሲሰጡ እንደተናገሩት በሀገራችን አሁን እየተተገበረ ያለው የትምህርት ስርዓት ሂደት በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት መሆኑን እና ከዚህ በመነሳት ያለንበት ዓለም የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተማሪዎችንም መምህራንንም የዲጅታል ቴክኖሎጂና የቋንቋ ክህሎቶቻቸውን በማጎልበት በኤሌክትሮኒክ ዘዴ በመታገዝ ትምህርቱን በቀጥታ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ስልጠናው መዘጋጀቱን አብራርተዋል:: የፕሮግራሙ ዓላማም እንደሀገርና እንደዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ለማድረግ፣ የተማሪዎችንና የመምህራንን አቅም ለመገንባት፣ የመልቲ ሚዲያ ማዕከል ለማቋቋም እና ሞዴል ዲጂታል ኮርሶችን ለማበልፀግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አስተባባሪው አክለውም በመርሃግብሩ በ50 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የቀጥታ ኢ-ትምህርት መስጠት ለማስቻል፣ 8 መቶ ሺህ ተማሪዎችን ኢ-ትምህርታዊ ፕላትፎርሙን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ 35 ሺህ መምህራንን ለማሰልጠን እና 5 መልቲ ሚዲያ ስቱዲዮዎችን ለመገንባት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ጠቀሜታውም ትምህርትን ለማዘመን፣ መማር ማስተማሩን ተደራሽና አካታች ለማድረግ፣ በአግባቡ መተግበር ሲጀምርም የሀገርንና ዩኒቨርሲቲዎችን ገፅታና እይታ እንደሚጨምር፣ የተማሪዎችን ወጪ እንደሚቀንስ፣ የመምህራንን ገቢ እንደሚያሳድግ እና በርካታ የስራ ዕድሎችንም እንደሚከፍት ገልፀዋል፡፡
በቀጣይ ቀናቶችም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና መምህራኖች ጋር ይሄንን የቀጥታ ኢ-ትምህርትን የተመለከተ ውይይት እንደሚካሄድና ቀጣይ አቅጣጫዎችም እንደሚቀመጡ ታውቋል፡፡