ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው ዙር በሰባቱም ካምፓሶች የተቀበላቸውን የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ማስፈተን ጀመረ::
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ እንደተናገሩት ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ እንደሀገር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ተፈታኞችን ተቀብሎ ያስፈትናል:: ፕሬዚደንቱ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሚያጠቡ እና መውለጃቸው የተቃረበ እናቶች በሚቀጥለው ዓመት እንዲፈተኑ ቢወሰንም እኛ ጋ የሚያጠቡ ጨቅላ ሕፃናት ይዘው የመጡ ተፈታኞች አጋጥመውናል ብለዋል:: ሴቶቹ ተፈታኞች እድላቸውን ለመሞከር እንችላለን ብለው ስለመጡ ዩኒቨርሲቲው ባለው የሕፃናት ማቆያ ውስጥ ድጋፍ ልናደርግላቸው ወስነን ተቀብለናቸዋል ብለዋል::
የተፈታኞችን ሁኔታ በተመለከተ ዘንድሮ የመጡት የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ከአምናው አንፃር በጣም የተረጋጉና ለፈተና የተሻለ ዝግጅት ያደረጉ መሆናቸውን አስተውለናል ብለዋል:: ሆኖም ግን አሁንም የተከለከሉ ነገሮችን ይዞ ለመምጣት የሞከሩ አልጠፉም:: "በርካታ ሞባይል ስልኮች በፍተሻ ወቅት ተይዘዋል: ለዘመድ ወዳጅ ለመፈተን የገቡ ሌሎች አካላትን ጭምር ለይተን በህግ ቁጥጥር ስር አውለናል:" ሲሉ ይሄን አይነት ድርጊት የሚፈፅሙ ሰዎች ከፍተኛ የሀገር ሀብት ፈሶበት የሰው ሀብት ተረባርቦ የሚሰራበትን ፈተና አልባሌና ህገወጥ ተግባራት በመፈፀም ለማበላሸት የሚሞክሩ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል::
ከሐምሌ 19 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚወስዱት ተማሪዎች 33,279 እንደሆኑ ታውቋል፡፡