ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለ24ኛ ጊዜ ከ7 ሺህ 5 መቶ በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛዉና ተከታታይ የትምህርት ፕሮግራሞች ከሁሉም ኮሌጆችና ኢንስቲትዩት የተዉጣጡ የመጀመሪያ፣ የሁለተኛና የሶስተኛ ድግሪ እንዲሁም ልዩ የድህረ ምረቃ ዲፕሎማ ሰልጣኞችን ጨምሮ 5,679 ወንድ እና 1,892 ሴት ተማሪዎቹን ለ24ኛ ጊዜ ሐምሌ13 ቀን 2015 ዓ.ም በዋናው ግቢ ስታድየም በደማቅ ስነ ሥርዓት አስመርቋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ለተመራቂ ተማሪዎችና ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኃላ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ 8 ኮሌጆችና 3 ኢንስቲትዩቶች 102 የመጀመሪያ፣ 141 የሁለተኛ፣ 55 የሶስተኛ ዲግሪ፣ 10 የህክምና ስፔሻሊቲ እና 1 ሰብ ስፔሻሊቲን ጨምሮ በአጠቃላይ 309 ፕሮግራሞችን በመክፈት ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሆነ ገልፀዋል::
ዶ/ር አያኖ የዛሬዉን ምረቃ ከሌሎቹ ጊዚያት ለየት የሚያደርገዉ የተለያዩ ዓለምአቀፍ እና አገር አቀፍ የሆኑ ፈርጀ ብዙ ተግዳሮቶችን ተቋቁመን ለስኬት በመድረሳችን ነዉ ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለዉም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ከተለየ በኃላ በመጪው አንድ ዓመት ተኩል ግዜ ውስጥ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እየሰራ እንዳለ ጠቁመዋል:: የዕለቱ ተመራቂዎች በተለይም የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከተጀመሩት ሃገራዊ የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያዎች መካከል አንዱ የሆነዉን የመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ መዉጫ ፈተና ወስዳችሁ ከ81% በላይ ማለፍ በመቻላችሁ ደስ ብሎናል ብለዋል።
የእለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዲሪ ቱሪዝም ሚኒሰቴር ሚኒሰትር እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክብርት አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው የዛሬዉን የምረቃ በዓል ልዩ የሚያደርገዉ ሃገራችን ባጋጠማት ዘርፈብዙ የዉጪና የዉስጥ ፈተናዎች ብዙዎች እንደፈሩት ሳትንበረከክ በልጆችዋ የተባበረ ክንድ በርካታ አንፀባራቂ ድሎችን ባስመዘገበችበት ወቅት ላይ በመሆኑ፤ በተለይ ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና መሰረት የሆነዉን ትምህርትና ሳይንሳዊ ምርምር ጥራቱን ለማስጠበቅ መንግስት እየወሰዳቸዉ ባሉ መጠነ ሰፊ የትምህርት ሪፎርም ስራዎች ዉስጥ ተፈትነዉና የመዉጫ ፈተናቸዉንም በብቃት ያለፉ ተመራቂዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ የምናስመርቅበት ልዩ ቀን በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አምባሳደሯ አክለዉም አንጋፋዉና ተመራጩ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዉስብስብና ተደራራቢ ጫናዎች ሳይበገር የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራውን ያለአንዳች መስተጓጐል አጠናክሮ በመቀጠል ለዚህ ስኬት መብቃቱ የአመራሩን እና የመላዉ ሰራተኞቹን ቁርጠኝነትና ትጋት የሚያሳይ ከመሆኑም በተጨማሪ ፈተናዎችን በፅናት የማለፍ ተምሳሌት መሆኑ በእጅጉ የሚያስመሰግነዉ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል:: በተጨማሪም የነገ ሀገር ተስፋ የሚወሰነዉ በሰለጠነ የሰዉ ኃይል በመሆኑ፤ ተመራቂ ተማሪዎችም በሚሰማሩበት መስክ ሁሉ ሀገርን በታማኝነት በማገልገል ለማህበረሰቡ ለዉጥ እንዲሰሩ አምባሳደሯ አደራ ብለዋል።