ሀዩ ከሜሪ ጆይ ጋር በትብብር ለመስራት ተፈራረመ

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ተፈራረመ፡፡

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ከተባለ አገር በቀል የተራድኦ ድርጅት ጋር በትምህርት፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በጤና ዘርፎች ወላጅ አልባና ተጋላጭ ህፃናትን፣ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሴቶችንና አረጋዊያንን ተጠቃሚ የሚያደርግና ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ፕሮጀክት ለማልማት እንዲሁም ለጋሽ አካላትን በማስተሳሰር ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችለው የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡

የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ስ/አስኪያጅ ሲ/ር ዘቢደር ዘውዴ እንደገለፁት ሜሪጆይ ኢትዮጵያ ተጋላጭ በሆኑ ህፃናትና ተንካባካቢዎች ላይ፣ በወጣቶች፣ በአረጋዊያን፣ በሴቶችና ከኤች.አይ.ቪ ጋር ከሚኖሩ ወገኖች ጋር በተያያዘ በጤና፣ በትምህርት፣ በመሰረታዊ የሰው ልጆች ፍላጎት፣ በሥርዓተ ፆታ፣ በኤች.አይ.ቪ በመሳሰሉት ላይ ትኩረት በማድረግ የድጋፍ፣ የእንክብካቤ፣ የህክምናና የማማከር እንዲሁም ሌሎች ስራዎችን በተለያዩ የሃገራችን ክልሎች እየሰራ የሚገኝ ሀገር በቀል ድርጅት ነው::

ሲ/ር ዘቢደር በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ወቅት ጨምረው እንደተናገሩት ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ ከተማም የአረጋውያን ማቆያ፣ የህክምና አገልግሎትና የወጣቶች ማሰልጠኛ ማዕከላትን በመገንባት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ በመሆኑ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለማልማት፣ ድርጅቱን ከሌሎች ለጋሽ አካላት ጋር በማስተሳሰርና የተለያዩ የምርምርና የማማከር ስራዎችን ለመስራት ፍቃደኛ በመሆኑ ምስጋዬ ላቅ ያለ ነው ብለዋል:: በተጨማሪም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት ሀዋሳ የተሰራው የወጣቶች ማዕከላችን ሕጋዊ ይዞታ እንዲኖረው ላደረጉት ታላቅ የመሪነት ሚና ከልብ አመስግነው ዩኒቨርሲቲው ካለው ማህበረሰብን የመደገፍ የቆየ ልምድ፣ የተማረ የሰው ኃይልና እውቀት አንፃር አብሮን በመስራት በሕብረተሰቡ ውስጥ ሌጋሲውን እንደሚያስቀጥል እንተማመናለን ብለዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት ከመማር ማስተማርና ምርምሮችን ከመስራት ጎን ለጎን በተለያዩ ዘርፎች ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ከተለያዩ ሀገሮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሀገር በቀልና አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን ገልፀው ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያም ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ከሴቶች፣ ወጣቶች፣ አረጋዊያን፣ ወላጅ አልባና ተጋላጭ ህፃናቶች ጋር በተያያዘ እየሰራ የሚገኘውን ስራዎች ዩኒቨርሲቲው በምርምር፣ በጥናት፣ ለጋሽ አካላትን በማፈላለግና በማስተሳሰር እንዲሁም በማማከር በጋራ ለመስራት ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ አክለውም አሁን ላይ በከተማም ሆነ በገጠሩ አካባቢ ብዙ ድጋፍ የሚፈልግ የማህበረሰብ ክፍል ቁጥሩ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ ከመሆኑ አንፃር ተቋማት ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ በመተባበር ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል:: ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ለማድረግ የተመሰረተ ድጋፍ ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች የቆመ ሃገር በቀል ተቋም በመሆኑ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ድርጅት ጋር ለመስራት ሁሌም ዝግጁ እንደሆነ ገልፀዋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et