የፈጠራና ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ

የቴክኖሎጂ ሽግግርና የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ማስተዋወቂያ አውደ ርዕይ አካሄደ::

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የዩኒቨርሲቲ- ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ስር የሚገኙ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን ለማስተዋወቅና በተሰሩት ፈጠራዎች ቀጣይ እድገት ላይ ለመወያየት በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ አውደ ርዕይ ተካሄዷል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምር/ቴክ/ሽ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ አውደርዕዩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት እንደ ሀገር መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር በተጨማሪ ከተሰጣቸው ተልዕኮ 60% የሚሆነውን ለምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ለማህበረሰብ ጉድኝት ስራዎች እንዲያውሉት መሆኑን አውስተው በሀገር ደረጃ የሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከዩኒቨርሲቲ- ኢንዱስትሪ ትስስር የቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግር ጋር መቀናጀት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለምርምር ከተለዩት ተቋማት አንዱ እንደመሆኑ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሸግግርና ፈጠራ ስራዎች ብዙ መስራት የሚጠበቅበት ስለሆነ ባለፉት ሶስት ዓመታት 5.2 ሚሊዮን ብር በመመደብ 29 የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች በተመራማሪዎችና ተማሪዎች እንዲሰሩ መደረጉንም ም/ፕሬዚደንቱ ጠቁመዋል:: ከነዚህም 12 የሚሆኑት ሥራዎች ሕጋዊ የባለቤት መብት እንዳገኙ ገልፀው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ የሚቀርቡትን ፈጠራዎች በመመልከትና በመጎኘት በቀጣይ ተሻሽለውና ውጤታማ ሆነው እንዲቀርቡ እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ተሳታፊዎች ገንቢ አስተያየታቸውን እንዲያበረክቱ አደራ ብለዋል፡፡

የቴክ/ሽግግርና የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ዶ/ር ባዩ ቡንኩራ በበኩላቸው የፈጠራ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር የእውቀት፣ ቴክኖሎጂና የሰው ልማት ምንጭ ሲሆኑ ባደጉት ሀገራት የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው እንደሚጠቀሙበት ገልፀው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ምን ለማከናወን እንደተቋቋመ፣ ዓላማውን፣ ምን እየተሰራ እንደሆነ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዴት እንደሚከናወን የጠራና የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ለተሳታፊዎች ገለፃ አድርገዋል:: እስካሁንም በተመራማሪዎችና ተማሪዎች የተለያዩ የሃይድሮሊክ ማሽኖች፣ የሙዝ/ እንሰት ቃጫ ማውጫ ማሽን፣ የቀበሌ ነዋሪዎች መረጃ አስተዳደርና ልውውጥ ስርዓት መተግበሪያ፣ የቱሪስት ቦታዎችና አገልግሎቶችን ለማሳየት የሚረዳ መተግበሪያ፣ የኤሌክትሪክ ተንሳፋፊ ቆሻሻ ውሃ ማጣሪያ ማሽን እና ሌሎችም በጉብኝቱ ወቅት የሚታዩ በርካታ የፈጠራ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው ተሳታፊዎችም የተሰሩ ፈጠራዎችን ከጎበኙ በኃላ ስለ ክፍሉ እና ፈጠራዎቹ ውይይት እንዲያደርጉ  እንዲሁም ያላቸውን ገንቢ አስተያየት እንዲሰጡ ጋብዘዋል፡፡

በፕሮግራሙ መሰረትም ተሳታፊዎቹ የፈጠራ ስራዎቹን በተለያዩ ቦታዎች ከጎበኙ በኃላ በተሰሩትና እየተሰሩ ባሉት የፈጠራ ስራዎች፣ ስራዎቹ እንዴት ወደ ተጠቃሚዎች መሸጋገርና ለዩኒቨርሲቲውም የገቢ ምንጭ መሆን እንደሚችሉ እንዲሁም ቀጣይ ተያያዥ ስራዎች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገው አውደ ርዕዩ ተጠናቋል::

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et