ራስ-ገዝነትን አስመልከቶ ከት/ሚ ጋር ዉይይት ተካሄደ

ትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲ ራስ-ገዝነትን አስመልከቶ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መማክርት ጋር ተወያየ፡፡

የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል አባላት ጋር በዩኒቨርሲቲ ራስ-ገዝነት ምንነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ አካሄደ፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲያችን በተልዕኮ ለምርምር ከተለዩት ስምንት የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን አስታውሰው ወደፊትም ራስ ገዝ ከሚሆኑት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ የዛሬው መድረክ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰዋል:: ስለ ራስ ገዝነት ምንነት፣ አስፈላጊነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለዩኒቨርሲቲው ካውንስልና ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መዘጋጀቱ ከዩኒቨርሲቲው ምን ዝግጅት ይጠበቃል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥና የሚሰጡንን ተልዕኮዎች በአግባቡ ለመተግበር እና ዓላማውን ለማሳካት ብዙ ይረዳናል ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚንስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በመክፈቻው ላይ እንዳስታወቁት የዩኒቨርሲቲ ራስ ነዝነትን በሚመለከት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተግባራዊ እንዲሆን በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንና ከዛም ተሞክሮ በቀጣይ በተለዩት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ ለማድረግ ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዎቹ ምን ምን ስራዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል የሚለውን በውይይትና በመግባባት ለማዳባር ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን አብራርተዋል:: በቀጣይ መድረክም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያከናውናቸውን ስራዎችና ዝግጅቶችን መገምገም እንደሚጠበቅ አሳውቀዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚ/ዲኤታው ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና በትኩረት መስኮቻቸው መለየት፣ የመውጫ ፈተናን ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ መስጠት እና የዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝነት ሂደትን ማረጋገጥ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል:: ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ የመፍጠር አስፈላጊነትን በመመካከርና በውይይት በማዳበር ወደተግባር እንደተገባ አውስተው በዚህ መድረክም የራስ ገዝ ምንነትና አስፈላጊነት ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ እንዲወጡ አልፎም እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ሃሳቡን በማውረድ ተቀራራቢ ግንዛቤን መፍጠር ዋናው የመድረኩ ዓላማ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ሳሙኤል አክለውም ራስ ገዝነት እውነትንና እውቀትን ለመፈለግና ለመግለፅ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሆነ: ዩኒቨርሲቲዎች አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ነፃነት በዋናነት እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀው ይሄንን ዓላማ ውጤታማ ለማድረግ ኃላፊነትን ከተጠያቂነትን ጋር ማረጋገጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ፣የዩኒቨርሲቲ ነፃነት ማሳያዎችና አውዶች፣ የተቋማት ነፃነት አስፈላጊነት፣ ራስ ገዝነት ማጣት ምን እንደሚያስከትል እንዲሁም ራስ ገዝነት እንዲሳካ ምን መሰራት እንዳለበት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በቀረበው የመወያያ ሰነድ ላይ ተሳታፊዎች በርካታ አስተያየትና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et