ለሴት ሰራተኞች የተግባቦት ክህሎት ስልጠና ተሰጠ

የማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ለሴት ሰራተኞች የተግባቦት ክህሎት ስልጠና ሰጠ::
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ለ50 ሴት አመራሮች: መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የሰው ለሰው እንዲሁም የአመራርነት ተግባቦት ላይ የአንድ ቀን የክህሎት ስልጠና ሰጥቷል::
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዘለቀ አርፍጮ ስልጠናውን አስመልክቶ እንደተናገሩት በኮሌጁ ብሎም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሴቶችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የዚህ አይነት ስልጠናዎች በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ ነው:: ከዚህም በላይ አሁን ላይ የሴት መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ቁጥር እያደገ ቢመጣም በተለያየ እርከን ወደ መሪነት የሚመጡት ውሱን መሆናቸው ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅብን አመላካች ነው ብለዋል::
የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እመቤት በቀለ በበኩላቸው ሴቶች የበለጠ የዚህ አይነቱ ስልጠና ማግኘት እንዳለባቸው ከግንዛቤ መወሰዱ ትክክለኛ አካሄድ ቢሆንም የተግባቦት ክህሎት ከዚህም ሰፋ ባለ መልኩ ለዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ሰራተኞች በየደረጃው መሰጠት እንዳለበት አመላክተዋል::
ስልጠናውን ያስጀመሩት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስርዓተ ፆታና ፀረ-ኤች አይ ቪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ምህረት ገነነ በበኩላቸው የማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ይሄን አይነት በጣም ወሳኝ አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ማዘጋጀቱ እጅግ እንደሚያስመሰግነው ተናግረዋል:: ብዙ ግዜ ሴቶች ወደ መሪነት ቦታ ሊመጡ ሲያስቡ ከሚያነሷቸው ችግሮች እንደ ትልቅ የአቅም ክፍተት የሚታየው የተግባቦት ክህሎት መሆኑን አስምረውበታል::
በሁለት አርዕስት የተከፈለውን ይሄንን የአንድ ቀን ስልጠና የሰጡት በአሰልጣኝነት: በተመራማሪነት እንዲሁም በመምህርነት ሰፊ ልምድ ያላቸው በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ት/ክፍል አንጋፋ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር መልሰው ደጀኔ ናቸው:: በስልጠናው የጠዋት መርሃግብር ላይ በሰው ለሰው ተግባቦት "Interpersonal Communication" ላይ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያስያዘ ገለፃ የተደረገ ሲሆን በከሰዓቱ ግዜ ደግሞ በአመራርነት ተግባቦት "Leadership Communication" ላይ ትኩረት ተደርጓል::
ዶ/ር ዘለቀና ወ/ሮ ምህረት ስልጠናውን ከማጠቃለላቸው በፊት የሰልጣኞችን ግብረ መልስ የተቀበሉ ሲሆን በስልጠናው የተሳተፉት ሴት ሰራተኞችም ባገኙት ዕድል እጅግ መደሰታቸውንና ወደፊት በያሉበት የስራ ክፍል የተሻለ አበርክቶ እንዲኖራቸው መነቃቃት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል::
የኮሌጁ ዲን በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለፁት ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሴት ሰራተኞቹን ወደ መሪነት ለማምጣት እንደዕቅድ ከያዛቸው መካከል መሰል የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን መስጠት እንደሆነ አንስተው የማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ በሁሉም ደረጃ ከሞጁል አስተባባሪነትና ቡድን መሪነት አንስቶ 50% በሴት ሰራተኞች እንዲሰራ ለማድረግ ይጥራል ብለዋል:: በመጨረሻም አሰልጣኙን ዶ/ር መልሰው ደጀኔን እና ይህንን አይነት ስልጠና ለመስጠት የተባበሩ አካላትን ሁሉ ካመሰገኑ በኃላ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ፕሬዚደንቱን ጨምሮ ያላቸውን አጋርነት አድንቀው ሌሎች መሰል ስልጠናዎችን ከውጭ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት እንዲሁም ስርዓተ ፆታና ኤች አይ ቪ ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጁ ቃል ገብተዋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et