ማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ በምርምርና ህትመት ጉዳዮች ዙሪያ ለኮሌጁ ምሁራን ወርክሾፕ አዘጋጀ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም በስሩ ላሉት መምህራን በምርምር ሥራዎች ላይ ተነሳሽነታቸውን ለመጨመር የሚያስችል የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዘለቃ አርፍጮ ስለፕሮግራሙ ሁኔታና አስፈላጊነት ዝርዝር መግለጫ ሲሰጡ ኮሌጁ በሰው ኃይል አቅም በጣም ሰፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለአብነት ሲጠቅሱ በእንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል ብቻ በቁጥር 25 ዶክተሮች መኖራቸውን ገልጸዉ በምርምሮችና ህትመቶች ዙሪያ በአቅማችን ልክ ስላልሠራን በቀጣይ በሰፊው ወደ ምርምሩ ሥራ በመግባት ምሁራኑ በዚህ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ረጅም የሚባል ልምድ ያለዉ ከመሆኑ አንጻር በርካታ ምርምሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ለሚሠሩ ሥራዎች ይረዳ ዘንድ የምርምር ጆርናሎችን መጨመር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ የማስፋፋት ተግባር መከናወኑን አስታውሰዋል፡፡ አክለዉም እነዚህ የምርምር ጆርናሎች ተደራሽ እንዲሆኑና ተመራማሪዎችም የምርምር ዉጤቶቻቸውን አሳትመው እንዲያሰራጩ አሁን ባለንበት ዘመን ጊዜዉ የሚፈልገውን የኦንላይን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለማህበረሰቡ ተደረሽ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡ በማስከተልም ኮሌጁ የምርምር ውጤቶችን በማሳተም ረገድ ተሳትፎው ዝቅተኛ በመሆኑ አሁን ባለው ደረጃ በዩኒቨርሲቲው 6ኛ ደረጃ ላይ መገኘቱን ጠቁመው ከዚህ በኋላ በየት/ክፍሉ ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዲኖር ጠንክሮ መሥራትና ለጥራትም ትኩረት መስጠት ተገቢ በመሆኑ ይህ የማስጀመሪያ መድረክ መሆኑን አስረድተዋል።