የትብብር ፕሮጀክቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት በግራንት ፕሮፖዛል አጻጻፍ እና የትብብር ስራዎች ላይ ስልጠና ሰጠ።
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚደንት ጽ/ቤት ስር የሚገኘው የትብብር ፕሮጀክቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ለዩኒቨርሲቲው ሲኒየር መምህራንና ተመራማሪዎች በግራንት ፕሮፖዛል አፃፃፍና የትብብር ሥራዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና በዋናው ግቢ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተሰጠ ነው።
የትብብር ፕሮጀክቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክተሩ ዶ/ር መብራቱ ሙላቱ ስልጠናውን አስመልክተው ሲናገሩ በዋነኝነት ሁለት አላማዎችን ይዞ የሚሰጥ መሆኑን ገለጸዋል:: ይሄውም በአንድ በኩል የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ስታፍ ለምርምርና ፕሮጀክቶች ማስፈጸምያ የሚሆን ሀብት በማፈላለግ አቅምን ማሳደግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሚካሄዱ የምርምር ስራዎች አለምአቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑና በዚሁ ዘርፍ ካሉ የሌሎች ሀገራት ባለሙያዎች ጋር የሚደረገውን የትብብር ምርምር ስራ ማሳደግ እንደሆነ ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም ስልጠናው ተግባር-ተኮር መሆኑንና ላለፉት ሶስት አመታት ለተለያዩ መምህራንና ተመራማሪዎች ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸው፤ ባለፈው አመት ይህንን ስልጠና የወሰዱ ተመራማሪዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ለግራንት ፕሮፖዛሎች የሚቀርቡ ጥሪዎች ላይ ካቀረቧቸው ሰባት የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎች መካከል በሶስቱ አሸናፊ ሆነውባቸዋል ብለዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቨርናንስና ልማት ጥናት ት/ክፍል መምህርና በፕሮጀክቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት የትብብር ፕሮጀክቶች ክትትልና ሪፖርቲንግ አስተባባሪ የሆኑት መምህር አካለወልድ ፈድሉ በበኩላቸው በዛሬው ዕለት "Grant Writing and Collaboration Skills" በሚል መሪ ቃል እየተሰጠ ያለው ይህ ስልጠና ዩኒቨርሲቲው በየአመቱ ከሚመድበው የምርምርና ፕሮጀክት ስራዎች ማስኬጃ በተጨማሪ ተመራማሪዎች በራሳቸው ጥረት ከአለም አቀፍ ተቋማት ፈንድ በማፈላለግ የሚካሄዱ የምርምርና ፕሮጀክት ስራዎችን ቁጥር ብሎም ጥራት ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። መምህሩ ጨምረው እንደገለጹት በዚሁ የትብብር ፕሮጀክት ስራ ልምድ ያካበቱ ተመራማሪዎች ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ልምዳቸውን በማጋራት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በዚህም የራሳቸውንና የዩኒቨርሲቲውን የዘርፍ አቅም ያሳድጉበታል ብለዋል።
እስከ ነገ ድረስ የሚዘልቀውን ይሄንን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና የሚሰጡት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ በዚህ ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት የካበተና እጅግ ስኬታማ ልምድ ያላቸው አንጋፋው መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሸለመ በየነ እንደሆኑ ታውቋል:: በስልጠናው ላይ ከሁሉም ኮሌጆች የተውጣጡ 55 መምህራንና ተመራማሪዎች ተካተዋል::
