በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሄደ።

“ስለ ሰላም ይገደኛል" በሚል መሪ ቃል ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ለዓለም የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ የማህበረሰብ የሰላም እሴት ግንባታና ፀረ ጥላቻ ንቅናቄ ላይ በማተኮር ከሚሠራው ሥራ ጋር በማያያዝ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አዘጋጅነት በዋናው ግቢ የሰላም ኮንፍረንስ ተካሂዷል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አዳቶ ሀገራችን ኢትዮጲያ ባለፉት አመታት በሰላም እጦት ስትቸገርና መንግስትም ህዝብም ተረጋግተው የየእለት ተግባሮቻቸውን በነጻነት መፈጸም ተቸግረው መቆየታቸውን ገልጸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት የሰላም ቁርጠኝነት በተወሰዱ እርምጃዎች አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል ብለዋል። አክለውም በአሁን ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሰላምን ዋጋ የተረዳንበት በመሆኑ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ከሰላም የሚገኘውን ትሩፋት ለመቋደስ እንድንችል ዩኒቨርሲቲው የሰላም ተምሳሌት ሆኖ ለመውጣት በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
 
የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ በበኩላቸው ሰላም ዋጋው የማይተመን መሆኑንና ያለ አስተማማኝ ሰላም ህብረተሰቡ ሰርቶ መግባት፣ ነግዶ ማትረፍ ብሎም መንግስት ደግሞ ኢንቨስትመንትን መሳብና ትኩረቱን በእድገትና ብልጽግና ላይ አድርጎ መስራት እንደማይቻል ስለሚታወቅ ሁሉም ህብረተሰብ የሰላም እሴቶችን በማጎልበት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል። አክለውው እንደገለጹትም የሲዳማ ክልል አዲስ የተመሰረተ ክልል እንደመሆኑ የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ቢሮው በርካታ ስራዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝና ከዚህም መካከል የሲዳማ ህዝብ ቀደምትና ባህላዊ የሆነውን "አፊኒ" የተሰኘ የግጭት አፈታት ስርዓት በማስፋፋት ከክልሉ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገኘውን ሰላም ለማጽናት እየተሰራ እንዳለ ታውቋል።
 
በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል ተማሪ የሆነችው ተማሪ ክርስቲያን ጸደቀ እኛ ተማሪዎች ነገ የምንረከባት ሀገር ሰላሟ የተጠበቀና በአብሮነት የጠነከረች ትሆን ዘንድ ዛሬ ላይ የምንወስደው እያንዳንዱ እርምጃ በምክንያታዊነት ላይ ብቻ ተመስርቶ መሆን እንዳለበትና የየትኛውም አካል አሉታዊ አጀንዳ ማስፈጸምያ ከመሆን መቆጠብ እንደሚገባ ገልጻለች።
 
በዕለቱ ከተከናወኑት በርካታ መርሀ ግብሮች መካከል አፊኖሎጂ ”AFFINOLOGY” ኢትዮጵያዊ የእርቅ ሥርዓት ባህላዊ ፍልስፍና ለቀጣይ ጥናት መነሻ ሀሳብ በአቶ አየለ አዳቶ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ የጂ አይ ዜድ ፕሮግራም አስተባባሪ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ያቀረቡ ሲሆን በሰላም እሴት ግንባታና ጸረ-ጥላቻ ንቅናቄና ግጭት አፈታት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ሰላም ተቋም ጋር በመተባበር ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተሰጠውን ስልጠና የወሰዱ 30 የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን እንዲሁም 30 ተማሪዎች "የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ተጠሪ" ተደርገው እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
 
የሲዳማ ክልል የመንግስት ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና ተማሪዎች የሰላም ኮንፍረንስ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et