የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በተለያዩ ምክንያቶች ያልተፈተኑ ተማሪዎችን ለሚፈትኑ መምህራን የፈተና ሂደቱን በተመለከተ ገለፃ ተደረገላቸው::
እንደ ሀገር የመጀመሪያው ዙር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሰጠ ሲሆን ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ያልተፈተኑ ተማሪዎች በሁለተኛው ዙር እንዲፈተኑ የተወሰነላቸው ከታህሳስ 18 እስከ 21/2015 ዓ.ም ለፈተና እንደሚቀመጡ ይታወቃል፡፡ ይሄንንም ተከትሎ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን እንዲፈትኑ የተመደቡ መምህራን የፈተና ሂደቱን በተመለከተ ታህሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ገለፃ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ተወካይ እና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ የፈተና ማዕከል ኃላፊ አቶ ቤካማ ስለሺ ገለፃውን የሰጡ ሲሆን ፈተኝ መምህራኖች ፈተና ክፍል ውስጥ ይዘው መግባት ከተፈቀደላቸው ቁሳቁስ ውጪ እንዳይዙ ህግና ስርዓቱን የጠበቀ ፈተና ለመፈተንና ስርዓቱን ለማስፈፀም መጀመሪያ ስርዓቱን መተግበር ከፈታኝ መምህራን እንደሚጠበቅ ጠቅሰው ከፈተና በፊት፣ ፈተናው ሲሰጥ እና ከፈተናው በኃላ መወሰድ ስለሚገባቸው የፈተና አፈታተን ስርዓቶችና ጥንቃቄዎች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
አክለውም በጋራ በኃላፊነት ከመስራት ጀምሮ ትኩረት በተሰጣቸው ዝርዝር ነጥቦች ላይ ገለፃ የሰጡ ሲሆን ባለፈው ፈተና ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ እርምጃዎችንም ለፈታኝ መምህራኖች አቅርበዋል፡፡
ፈታኝ መምህራኖችም በቀረበው ገለፃ በተነሱ ነጥቦች ላይ ውይይት በማድረግና ማብራሪያ በሚፈልጉት ላይም ጥያቄዎችን አንስተውና ለጠያቄዎቻቸውም መልስ ተሰጥቶበት ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡