የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የሰላም ግንባታን የሚያጎለብቱ ተማሪ ተኮር ፕሮግራሞችን አካሄደ።
የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ከኢትዮጵያ የሕግ ት/ቤቶች ማህበርና ከ International foundation for Electoral System ጋር በመተባበር የሰላም አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረጉ የተለያዩ የስፖርትና የጥበብ ስራዎችን በህግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አዘጋጅነት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የሚሳተፉበት የሩጫና የእግር ኳስ ውድድሮችና በሰላም ላይ ያተኮረ ዘጋቢ ፊልም ላይ ለመወያየት ከታህሳስ 15-16/2015 ዓ.ም በዋናው ግቢ ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡
የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደብረወርቅ ደበበ ይህ ፕሮግራም ከመዘጋጀቱ በፊት ለ20 የሕግ ተማሪዎች በሰላም አምባሳደርነት ላይ ስልጠና በመሰጠት እነዚህ ተማሪዎችም በሶስት ተከፍለው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንዲቀርፁ ባደረግነው መሰረት ተማሪዎቹ ካዘጋጁት ፕሮጀክቶች ላይ በመውሰድ በዩኒቨርሲቲያችን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተማሪዎች እንዲሳተፉ በማድረግ እንዲተገብሩት ታስቦ የተዘጋጀ ፕሮግራም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሕግ ትምህርት ቤት ኃላፊና መምህር አቶ በሃይሉ እሸቱ በፕሮግራሙ ላይ በሰላም ላይ ያተኮረ ዘጋቢ ፊልም ቀርቦ ተማሪዎችም በቀረበው ፊልም ላይ ለሰላም ግንባታ በሚረዳ መልኩ እንዲወያዩ መደረጉን፣ ለሰላም ግንባታ እንሩጥ በሚል መሪ ቃል የሩጫ ውድድር መካሄዱን እና የሰላም እግር ኳስ ውድድር መደረጉን ገልፀው በእነዚህ ሶስት እንቅስቃሴዎች የሰላም ግንባታ እና የሰላም አምባሳደርነት ፅንሰ ሃሳቦችን በማስረፅ የሰላም አምባሳደር ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው እንዲፈጠሩ አይነተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙም ላይ በሰላምን በተመለከተ እያዝናኑ ቁም ነገር የሚያስጨብጡ ግጥሞችና ዘፈኖች የቀረቡ ሲሆን ወደፊትም የዚህ መሰሉ ተግባር ተኮር እንቅስቃሴዎች ቀጣይነት እንደሚኖረው ከአዘጋጆቹ ለማወቅ ተችሏል፡፡