ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት ዝግጅት

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በርቀት መርሃ ግብር ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት ዝግጅት ማስጀመሪያ  አገር አቀፍ የምክክር መድረክ አዘጋጀ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሌሎች የትምህርት ልህቀት ማዕከል ማለትም ከአዲስ አበባ፣ ባህርዳር እና ጂማ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በርቀት መርሃ ግብር ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት ዝግጅት ማስጀመሪያ  አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ከታህሳስ 12-15/2015 ዓ.ም ለ4 ቀናት በቢሾፍቱ አዘጋጅቷል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት  ዶ/ር አያኖ በራሶ በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ ከሚገኙ ኮሌጆች አንዱ የሆነው የትምህርት ኮሌጅ የዩኒቨርሲቲውን አቅም በማስተባበርና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት እንደሀገር ተመርጦ  ከ9ኛ-12ኛ ክፍል እንዲሁም በተመረጡ ከ1ኛ-8ኛ ክፍሎች የተማሪ መማሪያና የመምህሩ መምሪያ መጽሐፍትን በማዘጋጀት ወደ ሙከራ ትግበራ እንዲገቡ ያደረገ ሲሆን የጎልማሶች ክህሎት ማሳደጊያ ሞጁሎችንም አዘጋጅቶ ወደ መጨረሱ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም በዚህ መድረክም ከዚህ በፊት የተዘጋጁትን መፅሐፍቶች በርቀት መርሃ ግብር ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት እንዲዘጋጁ ለማድረግ ካለፈው ዝግጅት የታዩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመለየት ጥራት ያላቸውን መፅሐፍት ለማዘጋጀት የሚራዳን የምክክር መድረክ ሲሆን ከዚህ በፊት ያሳያችሁትን ትጋትና ጥንካሬ  እንዲሁም የቡድን መንፈስ በዚህም ላይ በኃላፊነት እንድትደግሙት አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡

በኢ.ፌ.ድ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ ሽዋረገጥ ይህ ግብረ ሃይል ከዚህ በፊት የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በርካታ ሂደቶችን ያለፈ ሲሆን ከእነዚያ ሂደቶችም ብዙ ልምድና እውቀት ተምረንበታልና የአሁኑን በርቀት መርሃ ግብር ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት ዝግጅትም ይሄው ቡድን እንዲሰራው መወሰኑን ተናግረው  የስርዓተ ትምህርት ሂደት ተመጋጋቢና ተያያዥ በመሆኑ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀና ተደራሽ የሆነ መፅሐፍት ማዘጋጀት ለሰፊው ማህበረሰብ ጥቅሙ ብዙ በመሆኑ  በጥንቃቄ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ልዕቀት ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተከተል አዳነ በበኩላቸው ከዚህ በፊት የተሰጠንን ኃላፊነት ብዙ ችግሮችን በመቋቋም ለውጤት በማብቃታችን እንኳን ደስ አለን እያልኩኝ ካለፈው ብዙ ተምረንበታልና ይሄንን የትውልድ አደራ አሁንም በኃላፊነት ተቀብለን ለውጤት እንድናበቃው የሁላችንም ጥረትና ትጋት ያስፈልጋልና ሁላችንም ከዚህ ቀደም ያሳየነውን ትጋት እንድንደግመው አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡

በመድረኩም ከዚህ ቀደም በነበረው የመፅሐፍት ዝግጅት ሂደት ምን እንደሚመስል፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው እንዲሁም የርቀት ትምህርት መርሃ ግብር የመፅሐፍት ዝግጅት ሂደት ምን መሆን እንደሚገባው እና ተያያዥ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et