የወንዶ ገነት ኮሌጅ ባለሙያዎችን አስመረቀ

የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ በደን ልማትና አጠቃቀም ዙሪያ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ አስመረቀ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ በሲዳ ፕሮጀክት አማካኝነት ከኢትዮጵያ ደን ልማት ጋር በመተባበር ላለፉት 30 ቀናት በደን ልማትና አጠቃቀም እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሲዳማ እና ደቡብ ክልሎች የተውጣጡ 64 የደን ልማት ጣቢያ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ህዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም አስመርቋል፡፡

የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ተመራማሪና የሲዳ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር መሰለ ነጋሽ ይህ ስልጠና ከመዘጋጀቱ በፊት በኢትዮጵያ ደን ልማት አስተባባሪነት የሲዳ ፕሮጀክት በኮሌጁ ተመራማሪዎች አማካኝነት በደን ልማት ስርፀት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ጥናት በማድረግ በተገኘው ውጤት መሰረትም በደን ልማት ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የስልጠናውን ሞጆሎች በዘርፉ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እንዲያዘጋጁት ተደርጎ ስልጠናው እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር መሰለ አክለውም በስልጠናው ስለደን ልማት ስርፀት፣ ስለሰው ሰራሽ ደን ልማትና የተፈጥሮ ደን አያያዝ፣ የተጎዳ መሬትን ስለማከም፣ ስለ ጥምር ደንና እርሻ እንዲሁም የደን ውጤቶችን የገብያ ትስስር በመፍጠር የግብይት ሰንሰለትን ስለመዘርጋት በሰፊው ለባለሙያዎች ለአንድ ወር ስልጠና እንደተሰጠ ገልፀዋል፡፡

የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ምክትል አካዳሚክ ዲን ዶ/ር ሽመልስ ንጋቱ ያለፉትን ሰላሳ ቀናት በደን እና ተያያዝ ጉዳዮች በርትታችሁ በመሰልጠን ለዚህ ምረቃ ቀን ለበቃችሁ ተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩኝ ለዚህ ስልጠና መሳካት ጥረት ላደረጉት ለኢትዮጵያ ደን ልማት፣ ለሲዳ ፕሮጀክት፣ ለኮሌጁ መምህራንና አሰልጣኞች በኮሌጁና በራሴ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ደን ልማትከፍተኛ የደን ባለሙያ አቶ መስፍን ፀጋዬ ከወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ጋር በመሆን የዚህን መሰል ስልጠና ስንሰጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማና ደቡብ ክልሎች ለተውጣጡ ከ300 መቶ በላይ ባለሙያዎች ስልጠናው መሰጠቱን ገልፀው ወደፊትም አቅም በፈቀደ መልኩ ስልጠናው እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ተመራቂዎችም ባገኙት ስልጠና፣ በኮሌጁ አቀባበልና አገልግሎት አሰጣጥ መደሰታቸውን ገልፀው በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎትም ወደመጡበት ሲመለሱ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et