የስልጠና ረቂቅ ማንዋሎችን ለመገምገም አውደጥናት ተዘጋጀ

የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ሶስት የስልጠና ረቂቅ ማንዋሎችን ለመገምገም አውደጥናት አዘጋጀ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ በReREd ፕሮጀክት አማካኝነት ህዳር 17 ቀን 2015 ዓ.ም አውደጥናት አዘጋጅቷል፡፡ አውደጥናቱ የሚያተኩረው በታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች ተከላ እና ጥገና ላይ አጫጭር የስራ ላይ ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ ሶስት የስልጠና ረቂቅ ማንዋሎችን ለመገምገም መሆኑ ተገልጾአል፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሳሙኤል በቀለ እንደተናገሩት ኮሌጁ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ላይ ላለፉት በርካታ ዓመታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ አውስተው በሀገራችን ከኃይል አቅርቦት አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ ህብረተሰባችን ማገዶን እንደ  አማራጭ በመጠቀማቸው ምክንያት በደኖቻችን ላይ የመመናመን እንዲሁም በተጠቃሚዎችም ላይ የጤና እክል እያመጣ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በመሆኑም በታዳሽ ኃይል ላይ ጥናት በማድረግ ለሚመለከታቸው ባለሙያዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠት ተገቢ መሆኑ ስለታመነበት ስልጠናውን ለመስጠት በሚያስችሉ ረቂቅ የስልጠና ማንዋሎች ላይ ለመምከር የተዘጋጀ አውደ ጥናት መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

የኮሌጁ አካዳሚክ ዲንና የReREd ፕሮጀክት ኃላፊ ዶ/ር ሽመልስ ንጋቱ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በታዳሽ ኃይል ላይ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ሲሆን በኮሌጁ በሚገኙ  ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች በአነስተኛ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ዝርጋታና ጥገና፣ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን ተከላና ጥገና እንዲሁም የተሻሻሉ የምድጃ ንድፍ አሰራርና ብቃታቸውን አፈታተሽ ላይ ረቂቅ የስልጠና ማንዋሎች ተዘጋጅተው ለዘርፉ ባለሙያዎች እንዲገመግሙት የተላከላቸው በመሆኑ በዚህ አውደ ጥናት ላይ አጠቃላይ የግምገማው ግብረ-መልስ የሚቀርብበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም በፕሮግራሙ ላይ የሚሰጡ ግብዓቶችን እና አስተያየቶችን በማካተት በቀጣይ የተሟሉ ማንዋሎች ተዘጋጅተውና ተሰንደው ብቁ ሰልጣኞችን ለማፍራት አገልግሎት ላይ እንደሚውሉም ተናግረዋል፡፡

በአውደ ጥናቱም በሶስቱም ረቂቅ ማንዋሎች ላይ ግብረ-መልስ ከቀረበ በኃላ ውይይትና ገንቢ አስተያየቶች ተሰጥተው ፕሮግራሙ መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et