31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ  

ከሕዳር 8-10 2015 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶን ጨምሮ በርካታ የፌደራል፣ የክልል ባለስልጣናት እና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ሆነዋል።

ጉባኤው  በተለያዩ ንግግሮች ሲከፈት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ለእንግዶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 31ኛውን የትምህርት ጉባኤ ለመቀበል እድል በማግኘቱ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የተሳካ ቆይታ እንደሚኖራቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል። የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የ31ኛው ሀገር አቀፍ ጉባኤ ዋና አላማ በትምህርት ዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት በቀጣይ ምን አይነት አቅጣጫ እንከተላለን በሚለው ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን በንግግራቸው አስረድተዋል። የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ እንደ ሀገር 51 ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ሲሆን በእነዚህም ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በመጀመሪያው ቀን በተመሳሳይ ሰዓት በሁለት አዳራሾች ተከፍሎ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የአጠቃላይ ትምህርት ተቋማት ያለፈው ዓመት እቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ውይይትና ግምገማ ሲካሄድ ውሏል።

ጉባኤው በሁለተኛ ቀን ውሎው ከፍተኛ ትምህርትንና አጠቃላይ ትምህርትን በጋራ መድረክ ባገናኘበት በክብር እንግድነት የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ የትምህርት ሚኒስቴር እንደ ሀገር በትምህርት ስርዓቱ ላይ እያካሄደ ላለው ክለሳና ጠንካራ የሪፎርም ስራዎች የሲዳማ ክልል ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ክቡር ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ በበኩላቸው ትምህርት ትውልድ የሚታነጽበትና ሀገር የሚገነባበት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅና የረጅም ጊዜ ስራን የሚፈልግ መሆኑን አስገንዝበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ አራት ዋና ዋና ችግሮችን ለይቶ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝና እነዚህም ችግሮች የመምህራን የትምህርት አመራር ሙያዊ ብቃት ማነስ፣ በዘርፉ ውስጥ የሚስተዋለው ከፍተኛ የሞራል ስብራት፣ በትምህርት ዘርፉ የሚታየው ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እና በአካባቢያዊነት የፖለቲካና የአስተሳሰብ ምክንያት መተሳሰብ መሆናቸውን ገልጸው እንደ ሀገር ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ከገጠመን ጫና ሙሉ በሙሉ አለመላቀቅ እና ከጦርነት ጋር በተያያዙ ችግሮች በደረሱ በርካታ የትምህርት ቤቶች ውድመት የተነሳ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን በበቂ ፍጥነት ማስኬድ አለመቻሉን አብራርተዋል። በ2015 ዓ.ም ትኩረት ከሚሰጥባቸው ተግባራት መካከል የትምህርት ተደራሽነት ፍትሀዊነትን ባማከለ መልኩ እንዲሆን ማስቻል፣ የትምህርት ዲጂታላይዜሽንን ማስፋፋት፣ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በሁሉም የትምህርት ፕሮግራሞች ተግባራዊ ማድረግ፣ መምህርነት ትውልድ ብሎም ሀገር የመገንቢያ መንገድ እንደመሆኑ ብቃት ያላቸውን መምህራን ለማፍራት የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማትን አቅም ማሳደግ እና የዩኒቨርሲቲዎች ራስ-ገዝነትን ማረጋገጥ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ጉባኤውም በሚኒስትሩ ንግግር መነሻ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሸራሸር ውይይት ማካሄዳቸውም ታውቋል፡፡

በ3ኛው ቀን ውሎ በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ እንደተናገሩት በሀገራችን የትምህርት ስርዓት ላይ ለሚታየው ስብራት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም በዋናነት ከሚጠቀሱት ውስጥ በተማሪዎች ላይ የሚታየው በራስ ጥረትና ልፋት እውቀትን ከመሸመት ይልቅ ኩረጃንና መሰል መንገዶችን በመጠቀም ወረቀትን ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ፣ የመምህራን የእውቀትና ክህሎት ማነስ፣ እንዲሁም ምቹ ያልሆነ የመማር ማስተማሪያ ከባቢዎች እንደሚገኙ ታውቋል። አክለውም ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት የትምህርት ስርዓቱ ላይ መሰረታዊ የመዋቅር ለውጥ በማድረግ 1ኛ ደረጃ ትምህርትን እስከ 6ኛ ክፍል፣ መካከለኛ ደረጃን በ7ኛ እና 8ኛ ክፍሎች እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ከ9ኛ-12ኛ ክፍሎች በማድረግ እና የትምህርት ይዘት ወይም ካሪኩለም ላይ የነበረውን ችግር በመለወጥ በቀጣይ ከ9-12ኛ ክፍሎች አዲሱን የትምህርት ስርዓት ለማስጀመር ርብርብ በማድረግና የመምህራንን አቅም ለማብቃት በርካታ ተግባራት እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በሚቀጥሉት አምስትና አስር አመታት ውስጥ የሀገሪቱን የትምህርት ስርዓት በመሰረታዊነት ለመለወጥ አልሞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቁመው ለስኬታማነቱ ተማሪዎች የሚጠበቅብባቸውን ሁሉ ዝግጅት በማድረግ የለፉበትን ውጤት ብቻ ለማግኘት መስራት እንደሚጠበቅባቸው፣ መምህራን በእውቀትና ክህሎት እንዲሁም በስነ-ምግባር የታነጹ ተማሪዎችን ማፍራት እንዳለባቸው፣ ማህበረሰቡሞ ነገ ሊያይ የሚፈልገውን ለውጥ ለማየት ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልገው እና ሁሉም በየመስኩ ያሉ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዕለቱ የመምህራን ማህበር ሪፖርት ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት የተካሄደበት ሲሆን በተጨማሪም የትምህርት አጋር ድርጅቶች የድጋፍ ሞሽን ቀርቦ ጸድቋል። እንዲሁም በማጠቃለያው ጉባኤው በትምህርት ዘርፍ ባለፉት አመታት የታዩ ችግሮችን ለማረምና በቀጣይ የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል ተግባራዊ በሚደረጉ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ባለስምንት ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫ ነጥቦችን አውጥቷል፡፡

ከሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ የ12ኛ ክፍል ፈተና አፈጻጸም ሪፖርት ከየት/ም/ፈ/አ/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሼቱ ቀርቦ ከተደመጠ በኋላ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የተገኙ ዕድሎች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ በወቅቱ በቁርጠኝነት ሀላፊነታቸውን ለተወጡ የፌደራልና የክልል ተቋማት የዕውቅና አሰጣጥ መርሀ ግብር ተካሂዷል።

በመጨረሻም ትምህርት ሚኒስቴሩ በማሳረጊያው በልዩ ሁኔታ የአስተናጋጅነት ሚናውን የተወጣውን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን በመሸለም የዕውቅና ሰርቲፊኬት ከበረከተለት በኋላ ላለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ሲካሄድ የነበረው 31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ  ሕዳር 10 ቀን 2015 ዓ.ም በስኬት ተጠናቋል።

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et