ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምር/ቴክ/ሽግ/ም/ፕሬዝዳንት በማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አማካይነት መስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም በለኩ ከተማ አስተዳደር የምድረ ገነት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በዚሁ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ማርቆስ ፍሰሀ ንግግር ሲያደርጉ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎቱ በርካታ ተግባራት ላይ እንደሚሳተፍ ይኸውም በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ የሰብል ምርቶችን በማቅረብ፣ በእንስሳት እርባታ፣ የአከባቢ ጥበቃ እና በትምህርት ዘርፍ በልዩ ትኩረት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል። በትምህርቱ ዘርፍ ከሚከወኑ ተግባራት መካከል ተማሪዎች በመማሪያ ደብተር፣ በዩኒፎርም እና መሰል ለትምህርት አስፈላጊ በሆኑ ቁሳቁሶች እጥረት ከመማሪያ ገበታ እንዳይቀሩ ለማድረግ አቅመ ደካማ ወላጆች ያሏቸውን ተማሪዎች በመለየት የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም ተስፋ ባለመቁረጥና ሁልጊዜ የተሻለ ጥረት በማድረግ ከራሳችሁ አልፋችሁ ሌሎችን የምትረዱ መሆን ይጠበቅባችኋል በማለት ለተማሪዎቹ ምክር ለግሰዋል።

የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ር/መምህር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ዳኜ በበኩላቸው ት/ቤቱ በ1964 ዓ.ም በ6 መምህራንና በ350 ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን መጀመሩን አስታውሰው በዚህ ቆይታውም በርካታ ለአከባቢውና ለሀገር የተረፉ ተማሪዎችን ማፍራት መቻሉን ገልጸዋል። ትምህርት ቤቱ አሁንም በርካታ ተማሪዎችን እያስተማረ የሚገኝ መሆኑን ተገንዝቦ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል። 

የለኩ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ታደለ የምድረ ገነት ት/ቤት በክልሉ ከሚገኙ ቀደምት ከሚባሉ ትምህርት ቤቶች የሚጠቀስ ቢሆንም ላለፉት በርካታ አመታት ተገቢው ትኩረት ስላልተሰጠው ባስቆጠረው እድሜ ልክ ደረጃውን መጠበቅ እንዳልቻለ ጠቁመው ይህን ታሳቢ በማድረግ በትምህርት ቤቱ ነባር ተማሪዎች፣ መምህራን እና በህብረተሰቡ እንዲሁም በመንግስት ትብብር ትምህርት ቤቱን ለማዘመን እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የለኩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወኖ ቶሼ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ በዚህ ትምህርት ቤት አልፈው ትልልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ የቀድሞ ተማሪዎች ያስተማራቸውን ትምህርት ቤት ተመልሰው በመመልከት በሚያስፈልገው ሁሉ ሊያግዙ እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም ዛሬ ድጋፍ የተደረገላችሁ ተማሪዎች ትኩረታችሁን ትምህርት ላይ ብቻ በማድረግ ዛሬ የሚገጥማችሁን ችግር በማሸነፍ ነገ ለብዙዎች ምሳሌ ልትሆኑ ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የተደረገ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍን ተከትሎ የተማሪዎቹ ወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና መምህራን ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et