በወጣቶች ላይ የፖሊሲ አውደጥናት ተካሄደ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በወጣቶች ኑሮ፣ የስራ ሁኔታና የመኖሪያ ቤት ጉዳዮች ላይ የፖሊሲ አውደጥናት አካሄደ፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ አፍሪካው ዊትስ ዩኒቨርሲቲ እና ከእንግሊዙ ሼፊልድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን Youth Future በሚባል የትብብር ምርምር ፕሮጀክት አማካኝነት በወጣቶች ኑሮ፣ የስራ ሁኔታና የመኖሪያ ቤት ጉዳዮች ትስስሮች ዙሪያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ምርምር በማድረግ በጥናቱ ውጤት እና የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦች ላይ ለመምከር በመስከረም 9/2015ዓ.ም አውደጥናት አካሄደ፡፡

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ክቡር ረ/ፕ/ር ፀጋዬ ቱኬ በበኩላቸው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ እንደሀገር ከተጋረጡባት ዋና ዋና መሰናክሎች መካከል የስራ ዕድልና በከተሞች የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ተጠቃሽ ሲሆኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንደዚህ ባሉ የምርምር ውጤቶች የሚደገፉ ከሆነ ውጤታማ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በመክፈቻው ላይ እንደተናገሩት የምርምር ግኝቶችና ምክረ ሃሳቦችን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተደራሽ ለማድረግ ምርምሮችን ከሼልፍ በማውረድና ከአካዳሚያዊ ጠቀሜታቸው ባሻገር ለሀገር ልማትና ዕድገት አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው ለማድረግ መሰል የፖሊሲ ምክረ ሃሳብ ማበልፀጊያ መድረኮችን ማዘጋጀትና የምርምር ውጤቶችም ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ እንዲሆኑ ማስቻል ሀገራዊ አቅጣጫ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲያችን ይሄንን መድረክ ሲያዘጋጅ ኩራት ይሰማዋል ብለዋል፡፡

የኤፊዲሪ ከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ክብርት ወ/ሮ ሄለን ደበበ በመድረኩ ማስጀመሪያ ላይ ባቀረቡት መልዕክታቸው ላይ እንደገለፁት ለሰው ልጅ ከምግብና ከልብስ ቀጥሎ ያለው መሰረታዊ ፍላጎት የመጠለያ ፍላጎት ቢሆንም ቤት ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ መኖሪያ ብቻ ሳይሆን ዕሴት፣ የስራ ቦታ፣ መዝናኛ ስፍራ፣ የማህበረሰብ ማንነት ደረጃ መስጫ እና ሚኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም የጎላ ሃብት እንደመሆኑ መንግስት የሀገሪቷ አቅም በፈቀደ መጠን ለከተማ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤቶችን ለማቅረብ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ሄለን ይሄንን ካ በኋላ አሁንም በርካታ የቤት ስራዎች ይጠብቁናል ብለዋል፡፡

የኢፌዲሪ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ በበኩላቸው በመድረኩ የሚነሱት የፖሊሲ ግብዓቶች ኢትዮጵያ የወጣቶች ሃገር እንደመሆኗ እጅግ አስፈላጊ ነው ያሉ ሲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በዕውቀትና ሳይንሳዊ መረጃ ላይ የተመሰረቱ መሰል ግብዓቶችን ወደ ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዲቀየሩ ተግቶ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ቢሰራ አንዱ ችግር ለሌላኛው የመፍትኄ ዕድል ይሆናል ብለዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ ኃላፊ ዶ/ር ኢንጅነር እሸትአየሁ ክንፉ ደህሞ ጥናቱ በሁለት የአፍሪካ ሀገር ከተሞች ማለትም በሀዋሳ-ኢትዮጵያና ብሮንክሁትስፕረት-ደቡብ አፍሪካ ላይ ወጣቶችን በባለቤትነት ያሳተፈ ሲሆን በጥናቱም የወጣቶችን ኑሮ፣ የስራ ሁኔታና የመኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ ከዚህ በፊት የነበሩት ፖሊሲዎችን በጥልቀት በመፈተሸና በመዳሰስ ውጤቱ ምን እንደሚመስልና የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ለከፍተኛ የመንግስት አካላት፣ ለተመራማሪዎችና ለአጋር አካላት እያቀረብን ነው ያሉ ሲሆን በዚህ መድረክም የተለያዩ ምክረ ሃሳቦችን በመምከር ለመንግስት የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች ይቀርባሉ ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙም ላይ የተለያዩ የጥናት ውጤቶችና ምክረ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን በቀረቡት የጥናት ውጤቶች ላይም ውይይትና ምክክር ተደርጎ አውደ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et