መሞት አይቀርም መልካም ስራና ዝና ግን አብሮ አይቀበርም

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሐኪምና መምህር ለነበሩት እና በነሃሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም በድንገት ህይወታቸው ያለፈውን ዶ/ር ሙሉቀን ታምራትን ለማሰብ ኮሌጁ የደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላ እና የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓቶች ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም የኮሌጁ ከፍተኛ አመራሮች፣ የስራ ባልደረቦቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው እና ተማሪዎቻቸው በተገኙበት አካሂዷል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አንተነህ ጋዲሳ በፕሮግራሙ መክፈቻ ባልደረባችን ዶ/ር ሙሉቀን ታምራት በዩኒቨርሲቲያችን ከተማሪነት ጀምሮ በመምህርነት፣ በምርምር ስራዎችና ሰዎችን በፍቅር፣ በርህራሄና በትጋት በማከም በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ በኩላሊት ሕክምና በደቡብና ሲዳማ ክልሎች ብቸኛው ስፔሻሊስት በመሆኑ የሕክምና ሙያውን በብቃት ሲወጣ የነበረ በታካሚዎቹ፣ በተማሪዎቹ እና በእኛ ባልደረቦቹ የሚወደድ የነበረ ሲሆን በዶ/ር ሙሉቀን ድንገተኛ ሞት የተሰማን ሃዘን ጥልቅ መሆኑን እየገለፅኩኝ በዛሬው ዕለት ይሄንን ፕሮግራም ስናዘጋጅ እሱን ለማመስገን እና ለመዘከር እንዲሁም ሁላችንም የእሱን አርአያ በመከተል በሙያችን የተሰጠንን አደራ በአግባቡ እንድወጣ አደራ ለማለትና እሱ የጀመራቸውን ውጥኖች አርአያውን ተከትለን ከዳር እንድናደርሳቸው የበኩላችንን እንድንወጣ ለማሳሰብ ነው ብለዋል፡፡

በሕ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ መምህርና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ክንዴ ውብሸት እንደገለፁት ዶ/ር ሙሉቀንን ከማስተማር አንስቶ ህይወቱ ድንገት እስካለፈችበት በባልደረባነት ለበርካታ ዓመታት የማውቀው ሲሆን ከጠቅላላ ሐኪምነት ተነስቶ በኩላሊት ሕክምና ስፔሻላይዝድ በማድረግ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለይ በደቡብና ሲዳማ ክልሎችና ከአጎራባች ኦሮሚያ ክልል በበሽታው የሚሰቃዩ ታካሚዎችን ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይል የሚያገለግል ታታሪ ሐኪም፣ በተማሪዎቹም የሚወደድ እና ባለብሩህ አእምሮ ተመራማሪና ዕሩቅ ሃሳቢ የነበረ ነገር ግን በአጭሩ የተቀጨ ባልደረባ መሆኑ ታውቋል፡፡ አክለውም እሱን በማጣችን ብናዝንም በዛሬው ፕሮግራም የእሱን አርአያ በመከተል የደም ልገሳ በማድረግ የበርካቶችን ሕይወት ለመታደግና እሱን በመዘከር ለሌሎች ባለሙያዎችናተተኪዎች አርአያነቱን ለማስረፅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሟች ዶ/ር ሙሉቀን አባት አቶ ታምራት ሎንሰቆ በበኩላቸው ልጄ በምድር ላይ የቆየባቸው ሰላሳ አምስት ዓመታት ጥቂት ቢሆኑም አንድ ሰው ኖረ የሚባለው ለሌሎች ሲተርፍ ነው የሚለውን መርሁ በማድረግ ለበርካቶች ከፈጣሪ በታች በሕክምና ሙያው ሲደርስላቸው፣ ተተኪዎቹን ሲያስተምር፣ ሲመራመር፣ ሙያውን ለማሳደግና ተደራሽ ለማድረግ ሲጥር መቆየቱን በመገንዘብ  እሱን ለማሰብ የተማረበትና ያገለገለበት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕ/ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዚህን መሰል ፕሮግራም በማዘጋጀቱ ልባዊ ምስጋና እያቀረብኩኝ ደስታ በወርቅ ሽልማት ብቻ ሳይሆን በሞትም መኖሩን እና “መሞት አይቀርም መልካም ስራና ዝና አይቀበርም” የሚለውን በልጄ ተግባሮች አይቻለሁኝ ብለዋል፡፡ ባለቤቱ ወ/ሮ አይዳ ታደለም ይህ ፕሮግራም በእሱ ስም በመዘጋጀቱ እያመሰገንኩኝ በተለይ ስሙን ጠርተው ለማይጠግቡት ልጆቻችን አባታቸው በጣም ጥሩ፣ ምስጉንና ታታሪ እንደነበር የምናሳያቸው ሕያው ምስክርና ታሪክ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙም በተያዘለት ዕቅድ መሰራት የደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላ እና የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓቶች ተደርገው መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et