ለዩኒቨርሲቲው አመራሮችና መምህራን ስልጠና እየተሰጠ ነው

የልቦና ውቅር (ማይንድሴት) ትምህርት አስፈላጊነትና ምንነት ላይ ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና መምህራን ስልጠና እየተሰጠ ነው

ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና መምህራን ከደቡብ ኮርያ በመጡ አስልጣኞች የማይንድሴት ትምህርት አስፈላጊነትና ምንነት ላይ ስልጠና እንዲሁም በደቡብ ኮሪያ የአዲስ መንደር ግንባታ ንቅናቄ ላይ የተመሰረተ የልምድ ልውውጥ በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም እየተካሄደ ነው::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በፕሮግራሙ መግቢያ ላይ ሲናገሩ በማይንድሴት ትምህርት አስፈላጊነት ላይ እንዲሁም ደቡብ ኮሪያዎች በለውጥ ላይ ያላቸውን ልምድ ሊያካፍሉን በሀገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች እኛን መርጠው በመምጣታቸው እጅግ እናመሰግናለን ብለዋል:: ፕሬዚደንቱ እንግዶቹን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኃላ ተሳታፊዎችም ካገኘነው ትምህርትና ተሞክሮ በመነሳት እራሳችንና ተቋማችንን ለመጥቀም መጣር ይኖርብናል በማለት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን አመሰራረትና የእድገት ጉዞ አጭር ገለፃ አቅርበዋል፡፡

የስልጠና ቡድኑን ይዘው የመጡት የመንግስት አማካሪ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም በመክፈቻው ላይ እንደተናገሩት በዛሬው ዕለት እዚህ የተገኙበት ዋናው ምክንያት "እኛ በ1950 እና 60ዎቹ አካባቢ የነፍስ ወከፍ ገቢያችን ከደቡብ ኮሪያ የሚበልጥ የነበርን ወደ ኋላ ቀርተን ባለፉት 50 እና 60 ዓመታት ውስጥ ደቡብ ኮሪያዎች አድገው ኢኮኖሚያቸው ዓለምን እንዲመራ እንዴት ቻለ? እኛንስ ምን ጎተተን? ምንድነው የጎደለን? ማነው ይሄንን የለውጥ አስተሳሰብስ የሚወስደው?" የሚለውን ለመማማርና ልምድ ለመቅስም ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም በዚህ ትምህርት የተነቃቃና ከራሱ አልፎም ወደ ሌላው የሚያሰርፅ መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል:: አምባሳደሩ አክለውም ይህ የማይንድሴት ሃሳብ አንደኛ ተቋማዊ እንዲሆን በሁለተኛነትም አለም አቀፋዊ ሆኖ ተደራሽ እንዲሆን ነው የምንፈልገው በማለት ሃሳቡም ከራሳችን አልፎ በተቋማችን እና በትውልዳችን ሰርፆ የመጪው ዘመን ትውልድ የሚቀየርበት እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዶ/ር ቾይ ኦይ ቹል ይሄንን ስልጠናና ልምድ ልውውጥ በዋናነት በዩኒቨርሲቲያችሁ ለመስጠት የተገኘነው በዩኒቨርሲቲው ያለው የሰው ኃይል ያለው ተነሳሽነት ሃሳቡን ከመቀበል ባሻገር ለሌሎችም ለማስረፅ ተነሳሽነት ያላችሁ በመሆናችሁ ሲሆን የእናንተ አያት ቅድመ አያቶቻችሁም ከሰሜን ኮሪያ ጋር በነበረን የእርስ በእርስ ጦርነት 6037 የክቡር ዘበኛ ዘማቾችን ልካችሁልን ጀግንነታችሁን አሳይታችሁናልና እናመሰግናችኃለን በማለት ለእድገት ፀር የሆነውን የእርስ በርስ ግጭቶችን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ እና ያሏችሁ ሃብቶች ላይ ማተኮር አለባችሁ ሲሉ ለተሳታፊዎች ደቡብ ኮሪያ ከነበረችበት ድህነት አሁን ወዳለችበት ብልፅግና እንደደረሰች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በቀጣይም በቀረበው ትምህርት ላይ ውይይት ከተካሄደ በኃላ በከሰዓት በሚኖረው ፕሮግራም በደቡብ ኮሪያ የአዲስ መንደር ግንባታ እንቅስቃሴ ላይ የልምድ ልውውጥ ተደርጎ ጥያቄና አስተያየት ተቀብለው እያብራሩ ነው፡፡

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et