ሱሰኝነትን እንከላከል በሚል ርዕስ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጎጂ አደንዛዥ ንጥረ-ነገሮችን እና ሱሰኝነትን እንከላከል በሚል ርዕስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 15 ቀን 2014 በዋናው ግቢ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አዳቶ ከጎጂ አደንዛዥ ንጥረ-ነገሮችን እና ከሱሰኝነት ጋር በተያያዘ ለትውልድ የሚተርፍ ውይይት አድርገን የመፍትሄ አቅጣጫ ካላመጣን ትውልዱ እየተበላሸ እና ሀገር ተረካቢ እያጣች እንደሆነ ገልፀው ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር ተያይዞ ትውልዱ በአደንዛዥ አስተሳሰብ ውስጥ በመዘፈቅ ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ እየገባ የአጥፊዎች መሳሪያ በመሆን በህዝባችን መካከል ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት እንዳይኖር በማድረግ በምትኩ የነበሩ አንድነቶችና መተባበሮች እየጠፉ፣ አመፅ የበዛበት ሰው በአስተሳሰቡ፣ በዘሩ፣ በቋንቋው እና በብሄሩ እየታደነ የሚገደልበት ደረጃ ላይ የደረስን በመሆኑ ካሁኑ መፍትሔ ካላበጀንለት የምንመኘውን ብልፅግና ማምጣቱ ቀርቶ ሃገር አፍራሽ ትውልድ ይበረክታል ብለዋል፡፡

የሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶችና ኤች.አይ. ቪ ኤድስ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ምህረት ገነነ በበኩላቸው ሀዋሳ ከተማ ውብና ማራኪ ብትሆንም ተማሪዎቻችን ብሎም በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች እንደመሆናቸው በሌሎች ነገሮች ከመዝናናት ይልቅ  በተለያዩ ምክንያቶች በመሳብ ወደ ሱስ ውስጥ ይገባሉ፡፡ መልካም ስነ ምግባር ያለው፣ ለራሱ እና ለሀገር የሚጠቅም ትውልድ ለማፍራት ከእኛ ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል የሚለውን በመምከር የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ሀገር አቀፍ ሴት ወጣቶች በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሪት ማርታ ማሙዬም እንዲሁ በመድረኩ በአደንዛዥ ዕፅ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በችግሮቹ እና መፍትሔዎቹ ላይ በጋራ በመምከር ሁሉም ባለድርሽ አካላት በባለቤትነት ጉዳዩን የራሱ አድርጎት እንዲሰራው ውይይትና ምክክር ለማድረግ የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የኃይማኖት አባቶች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ በመወያየትና በመምከር መፍትሔ ነው ያሉትን ሃሳቦች በመድረኩ አንስተው ፕሮግራሙ መጠናቀቁን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et