የስርዓተ ትምህርት ውጫዊ ግምገማ ዙሪያ የስልጠና ወርክሾፕ አዘጋጀ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የትምህርት ኮሌጅ በቅንጅት የስርዓተ ትምህርት ውጫዊ ግምገማ እና በአይ.ሲ.ቲ፣ በስርዓተ ጾታና አካቶ ትምህርት ዙሪያ የስልጠና ወርክሾፕ አዘጋጁ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የትምህርት ኮሌጅ ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓ.ም በጋራ ባዘጋጁት በዚሁ ወርክሾፕ ላይ የNURTURE ፕሮጀክት አባላት የሆኑት የጎንደር፣ ጅማ፣ ደብረ ማርቆስ፣ አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ሁለት የኖርዌይ ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች ከባህር ማዶ ተሳታፊዎች ሆነዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ፍሰሀ ጌታቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካሪኩለሞች ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ እውቀት፣ በተግባራዊ ችሎታ፣ በአዕምሮ ብስለትና ማህበራዊ ሀላፊነት የበቁ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሆነው መቀረጽ እንደሚገባቸው ገልጸዋል። በNURTURE ፕሮጀክት ስር በትምህርት ቴክኖሎጂና ፈጠራ የሁለተኛ ዲግሪ መርሀ ግብር ለመጀመር ሲደረግ የነበረው የካሪኩለም ቀረጻ ተጠናቆ ለውጫዊ ግምገማ የቀረበ መሆኑን እና ከዚህም ግምገማ የሚገኙ ገንቢ ሀሳቦችን በማካተት በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ወደ ትግበራ ይገባል ብለዋል።

የሀዋሳዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ፋሲካ ቤቴ በበኩላቸው የNURTURE ፕሮጀክት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሀገር ውስጥ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች በአባልነት የሚገኙበት መሆኑን ገልጸው በዚህ ፕሮጀክት ስር ከሚደረጉ ስራዎች መካከል አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን በሁለተኛ ዲግሪ እና በፒ.ኤች.ዲ ደረጃ ማስጀመር መሆኑን አብራርተዋል። ቀደም ሲል በጎንደርና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች በፕሮግራሙ ስር ሁለት አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች መጀመራቸውን አንስተው በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ መልኩ የሚጀመረው የትምህርት መርሀ ግብር ሶስተኛው መሆኑን ተናግረዋል።

የNURTURE ፕሮጀክት አስተባባሪና ከኖርዌዩ South East University የመጡት ዶ/ር ሸጋው አናጋው ስለ NURTURE ፕሮጀክት አላማ በገለጹበት ወቅት እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በNORHED-II ፕሮግራም ስር የሚገኝና አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞችን መክፈት፣ የአቅም ግንባታ፣ የጾታዊ እኩልነት እና አካታችነት እንዲሁም የትምህርት ዘርፉን ከኢንደስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር ዙሪያ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ለ6 አመታት በሚቆይበት ወቅት  የአቅም ግንባታን በማሳደግ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለመፍጠር በማሰብ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ እና በእስካሁኑ ጉዞውም ውጤታማ ስራዎችን መስራት ተችሏል ብለዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና ትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ብርሀኑ ሙረዳ በበኩላቸው ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመምህራንን አቅም ማሳደግ በትምህርት ሴክተሩ እንደ ሀገር የታሰበውን እቅድ ለማሳካት እና የበቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም የሁለተኛ ደረጃ መምህራንን እውቀት እና ችሎታ ለማሳደግ መሰል አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች የሀገራችንን ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተቀርጸው ሊዘጋጁና በፍጥነት ወደ ትግበራ ገብተው ውጤት ሊያመጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et