የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ አመታዊ የምርምር ጉባዔ አካሄደ

የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ አመታዊ የምርምር ጉባዔ አካሄደ፡፡

በወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን ፅ/ቤት ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሌጁ መምህራን የተሰሩ 13 የምርምር ውጤቶችን ለመገምገምና በቀጣይም ጎልብተው እና ዳብረው ተሰርተው በህትመት መልክ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችል አመታዊ የምርምር ጉባዔ በመጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም አካሄደ፡፡

የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሞቱማ ቶሌራ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በዚህ ዓውደ-ርዕይ ተመራማሪዎች የሰሯቸውን ምርምሮች አቅርበው በማስተቸት ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለማሳደግና ለማሳተም ግብዓት የሚያገኙ ሲሆኑ ተሳታፊ መምህራን ደግሞ ከሌሎቹ ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ በቀጣይ ለሚሰሩት የምርምር ስራዎች ይገለገሉበት ዘንድ ጉባዔው ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ኮሌጁም በምርምር ዘርፍ ምን ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ ለመፈተሸና ለሚያሳትመው የምርምር ጆርናል ግብዓት ለማግኘት መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ዲኑ ”የምርምር ዩኒቨርሲቲ እና አንጋፋ እንደመሆናችን በምርምርና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ብዙ የሚጠበቅብን በመሆኑ የኮሌጁ መምህራን ምርምር ላይ ትኩረት በማድረግ ተግተው እንዲሰሩ አደራ እላለሁ“ ብለዋል፡፡

የኮሌጁ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን ዶ/ር ክብረስላሴ ዳንኤል እንደተናገሩት በዚህ ፕሮግራም በሚቀርቡት የምርምር ውጤቶች ላይ አስተያየቶችና ግምገማ በማካሄድ በቀጣይ እንዲዳብር፣ የሌሎችን መምህራን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ተመራማሪዎች የገጠሟቸውን ችግሮች በመለየት ለወደፊቱ አቅጣጫ ለማስያዝ የታለመ ጉባዔ መሆኑን ገልፀው መምህራን ምንም እንኳን ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ችግሮቹን በመጋፈጥ ከምርምር ውጤት የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በማሰብ ተግተው ምርምሮችን እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በፕሮግራሙም ላይ የተለያዩ ምርምር ውጤቶች ለተሳታፊዎች ቀርበው ውይይትና ገንቢ አስተያየቶች ከተሰጠባቸው በኋላ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et