ክቡር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አመራርና መምህራን ጋር ውይይት አካሄዱ

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አመራርና መምህራን ጋር ውይይት አካሄዱ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አመራርና መምህራኖች ከትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ከሚመለከታቸው ሚኒስትር ድኤታዎች ጋር በወቅታዊ ትምህርት ጥራት፣ ተግዳሮቶችና እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ምክክርና ውይይት አካሂደዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ወቅት ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስከደረሰበት ድረስ ያለውን ታሪካዊ ዳራ አውስተው በአሁኑ ሰዓትም የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ ትኩረት በማድረግ  104 የመጀመሪያ፣ 141 የሁለተኛ፣11 የሰብስፔሻሊቲና ስፔሻሊቲ እንዲሁም 54 የሶስተኛ ድግሪ ፕሮግራሞችን ከፍቶ በማስተማር ላይ እንደሆነ ገልፀው የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትርና ሚኒስትር ድኤታዎች ከዩኒቨርሲቲው አመራርና መምህራኖች ጋር ለመወያየትና ለመምከር በመገኘታቸው በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስም ልባዊ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በውይይቱ ላይ ባለፉት አራት ወራት በተደረገው ጥናት ውጤት መሰረት በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት መውደቁን፣ የትምህርት ተቋማት ከክልላዊነት መላቀቅ አለመቻላቸው እና የደረሰብን የሞራል ክስረትና ውድቀት የጎላ መሆኑን ገልጸው ከዚህም አዙሪትና ውድቀት ለመውጣት ትምህርትና ፖለቲካ መነጣጠልና የትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ መምህራኖችና ሰራተኞች ሹመትና ቅጥር ዕውቀትና ችሎታን መሰረት ማድረግ እንዳለበት፣ ተቋማዊ ነፃነት ወሳኝ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ ማስቻል ላይ እየተሰራ እንደሚገኝ እንዲሁም ከዚህ በኃላ የሚሰጡ ድግሪዎች የመውጫ ፈተና እንደሚያስፈልጋቸውና በትምህርት ስርዓቱ ላይ ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሁሉም የለውጡ አካል በመሆን ትብብራችሁን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

እንዲሁም በት/ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚ/ር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የትምህርት ሴክተር ሰፊ በመሆኑ ቅደም ተከተል በማበጀት በትምህርት ፖሊሲዎች ላይ፣  ተቋማዊ ነፃነት እና አወቃቀር ላይ፣ የመምህራን መብትና ግዴታዎች እንዲሁም የመምህራን ምዘና ስርዓታችን ልምድንና የተመዘገበ ስኬትን ያማከለ ዕድገት እንዲኖረው እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በት/ሚኒስትር የአጠቃላይ ትምርት ዘርፍ ሚ/ር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ የገጠሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋምና ችግሮችን በመፍታት ሀገርን በማሻገር ሂደት ላይ የራሱን አሻራ ያሳረፈ መሆኑን ገልፀው ሁላችሁም የእኛ ልጆች ወደፊት ምን ይሉናል ብላችሁ በትምህርት ስርዓቱ ላይ የራሳችሁን ድርሻ እንድትወጡ አደራ እላለሁኝ ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱና ገንቢ አስተያየቶችን  የሰነዘሩ ሲሆን ክቡር ሚንስትሩም ከተሳታፊዎች ጋር በመወያየት እና ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሾችን በመስጠት ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et