ቢ.ጂ. አይ ኢትዮጵያ ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሙያ ክህሎት ልምምድ ለመስጠት ፕሮግራሙን ይፋ አደረገ፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ቢ.ጂ. አይ ኢትዮጵያ ባደረጉት የጋራ ስምምነት መሰረት በሀገራችን ውስጥ ግዙፍ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ቢ.ጂ. አይ ኢትዮጵያ ፍላጎት ያላቸውን የዩኒቨርሲቲውን የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎችን ለማብቃትና የሙያ ክህሎት ልምምድ ለመስጠት ኤክስ.ፒ የተሰኘ የሙያ ክህሎት ፕሮግራም አዘጋጅቶ የካቲት 18 ቀን 2014 ዓ.ም ለተማሪዎች ይፋ አደረገ፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ባዩ ቡንኩራ በተግባር ልምምዱ ወቅት የፈጠራ ችሎታና ብቃት ያላቸው ተማሪዎች የኢንዱስትሪውን ችግሮች በመለየትና በመፍታት እንዲሁም የኢንዱስትሪውን የምርምር ክፍተት ለዩኒቨርሲቲው ሪፖርት የሚያደርጉ ሲሆን ኢንዱስትሪውም ብቃት ያላቸው ምሩቃንን በመለየት ውጤታማ ቅጥር ለመፈፀም እድል ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የቢ.ጂ. አይ ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ዮናስ ገመቹ የፕሮግራሙ ዓላማ የስራ ዕድል ክፍተትን ለመሙላት፣ የስራ አካባቢን ለተማሪዎች ለማለማመድና ክሎታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም ለሌሎች ድርጅቶችም አርዓያ ለመሆን መሆኑን ገልፀው መስፈርቱን የሚያሟሉ የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች በየዓመቱ እስከ ምርቃታቸው ድረስ ሁለት ወራትን ከአምስቱ የቢ.ጂ. አይ ኢትዮጵያ ፋብሪካዎች በአንዱ ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ ተከታታይ የሙያ ክህሎት ልምምድ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙም ላይ ስለ ቢ.ጂ. አይ ኤክስ.ፒ መርሃ ግብር ምንነት እና ተማሪዎች በቢ.ጂ. አይ ኤክስ.ፒ ተሳታፊ ለመሆን ምን እንደሚጠበቅባቸው ገለፃና ውይይት የተካሄደ ሲሆን በፕሮግራሙ ልምምድ ሂደት የላቀ ውጤት ለሚያስመዘግቡና ችሎታቸውን ለሚያስመሰከሩ ተማሪዎች ከልምምዱ በኃላ ድርጅቱን እንደሚቀላቀሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡