የመጀመሪያ ዓመት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ መረጡት ኮሌጆች ሲሄዱ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ትውልድ ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እና ባሉት ሰባት ካምፓሶችም የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ከ45 ዓመታት በላይ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን በ2013 ዓ.ም አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ በዋናው ግቢ ሲያስተምር ከቆየ በኃላ የመጀመሪያ ዓመት ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ 2672 ተማሪዎችን እንደየምርጫቸውና እንዳመጡት ውጤት መሰረት ድልድል አካሄደ፡፡
የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሞቱማ ቶሌራ እንደተናገሩት ወደኮሌጃችን 320 ተማሪዎች ተመድበው በ12 የት/ክፍሎች ለመማር የመጡ ሲሆን ኮሌጁም አስፈላጊውን ዝግጅት በመኝታ፣ ምግብ፣ ላይብረሪ፣ ቤተ-ሙከራ እና የትምህርት ፕሮግራም ለመምህራኖችና ተማሪዎች በማውጣት ያዘጋጀ መሆኑን ገልፀው ተማሪዎችም ከየካቲት 16 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርታቸውን በርትተው መማር እንዳለባቸውና የኮሌጁ ማህበረሰብም ለተማሪዎቹ የተቻለውን እንዲያደርግ ጥሪያቸውንን አቅርበዋል፡፡
የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ወገኔ ማርቆስ ከዚህ በፊት በነበሩ 374 ነባር ተማሪዎች ላይ በጦርነት ከተጎዱት መቀሌና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች 174 ተማሪችን ተቀብለን እያስተማርን ሲሆን አሁን ደግሞ 300 አዲስ ተማሪዎችን በ7 የትምህርት ክፍሎች ለማስተማር ተቀብለናል ካሉ በኃላ ተማሪዎቻችንንም ከመቀበላችንን በፊት የቀድሞ ስራዎቻችንን በመገምገም በቀጣይ ትኩረት የሚስፈልጋቸውን በመለየት ለአዲሶቹ ተማሪዎችም የመምህራን ድልድል፣ የምግብ፣ መኝታ፣ ላይብረሪ እና መዝናኛ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ የተደረገ ሲሆን በቅርቡም ዲጅታል ላይብረሪ ለመጀመር ኮምፒውተሮች ተዘጋጅተው የኢንተርኔት ዝርጋታ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልፀው አዲሶቹ ተማሪዎችም ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ትውውቅና ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የበንሳ ዳዬ ካምፓስ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሬው ካሳ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በነበሩት ተማሪዎች ላይ 263 ተማሪዎችን ለማስተማር በካምፓሱ በኩል የመማር ማስተማር፣ የመኝታ፣ ምግብ፣ ላይብረሪ እና ላብራቶሪ አገልግሎት ለመስጠት ሁሉም ዝግጁ መደረጉን ገልፀው በተደረገው ጥናት መሰረት የስራ ዕድል የሚገኝባቸውን የአግሮ ኢኮኖሚክስና ኮምፒውተር ሳይንስ የትምህርት ክፍሎችን እንደአዲስ በመክፈት በ8 የትምህርት ክፍሎች ለማስተማር መዘጋጀታቸውን እንዲሁም ካምፓሱ የተጀመረው ግንባታ ቢጠናቀቅ እና የውሃ አቅርቦትም በሚፈለገው ልክ ቢስተካከል ወደፊት ወደ ዩኒቨርሲቲ ማደግ የሚችል ግቢ በመሆኑ የተማሪዎቹ ቁጥር መጨመር ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከሪጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት በተገኘው መረጃ መሰረትም በዋናው ግቢ፣ ግብርና ኮሌጅ፣ በሕክምናና ጤና ሳይንስ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ተማሪዎቹ መደልደላቸውን ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተያያዘ ዜናም በጦርነት ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉትን ከመቀሌና አክሱም ዩኒቨርሲቲ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡትን 1096 ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲው ተቀብሎ ከታህሳስ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡