የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ላይ የምክክር ዓውደ-ርዕይ አዘጋጀ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ከምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ጋር በጋራ በመሆን በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ተሞክሮዎች፣ ተግዳሮቶችና ወደፊት መወሰድ ባለባቸው እርምጃዎች ላይ ለመወያየት በየካቲት17/2014ዓ.ም የምክክር ዓውደ-ርዕይ አዘጋጀ፡፡
የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንትየሆኑት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በምክክር መድረኩ እንደተናገሩት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 50ኛ የወርቅ እዮቤልዩ ሊያከብር 4 ዓመታት ብቻ የቀሩት አንጋፋና በቅርቡም የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከተለዩት አንዱ ሲሆን በቀጣይም በርካታ ችግር ፈቺ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በተለይ በግብርና፣ ጤና፣ በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች እንድናበረክት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ታፈሰ በማስከተልም እንደገለፁት እንደሀገር አንድ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ከተሰጡት ተልዕኮዎችና መዋዕለ ንዋይ 40 ያህል ድርሻውን ለምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ማዋል እንዳለበት እና እንደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም ማንኛውም መምህር ይሄንን ተግባራዊ በማድረግ በሁለት ዓመት ውስጥ ቢያንስ አንድ የምርምር ውጤት ማበርከት እንዳለበት መቀመጡን ገልፀው የዛሬው የውይይት ዓላማም የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ካለው የተማረ የሰው ኃይልና መሰረተ ልማት አንፃር ለምን የሚጠበቅበትን ያህል የምርምር ውጤቶች አላበረከተም የሚለውን ለመፈተሽ፣ እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም ለማስቀመጥ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ዳኜ ሽብሩ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት እንደ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በዕውቀት፣ አመለካከትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይም ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችን መስራት የሚጠበቅብን ሲሆን ኮሌጁ በርካታ ነባርና አንጋፋ ምሁራን፣ቤተ-ሙከራዎችና ማዕከሎች ቢኖሩትም በሚፈለገው ልክ የሚጠበቅበትን የምርምር ውጤቶች እያበረከተ ባለመሆኑ እና የተሰሩ ምርምሮችም በተደራጀ መልኩ ሪፖርት ተደርገው መሰነድ ባለመቻላቸው ችግሩ ምን እንደሆነ ከኮሌጁ መምህራን እና ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመምከር ለችግሩም እልባት ለመስጠት የተዘጋጀ የምክክር መድረክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በፕሮግራሙም ላይ የኮሌጁ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ፅ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር መለሰ ማዳ ስለኮሌጁ የምርምር ውጤቶችና ህትመቶች፣ የታዩ ክፍተቶች በመድረኩ መነሳት ስላለባቸው ነጥቦች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን የኮሌጁ ምሁራንም በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን እና መፍትሄ ያሏቸውን ሃሶቦች በመድረኩ መወያየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡