በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በሀዋሳ ከተማ ለ3 ቀናት የሚቆይ የማህበረሰብ ቀን ፌስቲቫል አካሄደ፡፡
ዳይሬክቶሬቱ በዚህኛው መርሀ ግብሩ ትኩረቱን ያደረገው የስኳር፣ የደም ግፊትና ከልክ ያለፈ ውፍረት መለየትና ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ወንድወሰን ሺመልስ ከፌዴራልና ከክልል መንግስታት የጤና ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተካሄደ መርሀ ግብር መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ 6 ወራት ውስጥ በሲዳማ ክልል በገጠር አካባቢዎች የሚኖረውን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
በእነዚህ ቀናት ውስጥ በሚካሄደው የነፃ ምርመራ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወደ 2 ሺህ ገደማ የሚሆኑ የሀዋሳ ከተማ ማህበረሰብ አባላት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን በአንጻሩ በመርሀ ግብሩ ላይ ከተገኙት መካከል እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ስለመሆኑ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡