በተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በፕሮግራም ጥራት ኦዲት ላይ ስልጠና ተሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በፕሮግራም ደረጃ በፕሮግራም ጥራት ኦዲት መመሪያዎች፣ መገምገሚያ ነጥቦችና ደረጃዎች እንዲሁም የመገምገሚያ ሰነድ አዘገጃጀት ዙሪያ ለኮሌጁ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እና መምህራኖች በወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ በህዳር3/2014 ዓ.ም ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ዶ/ር ዘይቱ ጋሻው የተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ኮሌጁ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ድግሪ ድረስ በርካታ ፕሮግራሞችን ከፍቶ ተማሪዎችን እያስተማረና እያስመረቀ ቢሆንም እየተሰጡ ያሉ ፕሮግራሞች ጥራትና ውጤታማነታቸው፣ የምሩቃን ተፈላጊነት፣ብቃትና ያሉበት ደረጃ፣ የቀጣሪዎችና ገበያ ፍላጎት፣ ስራ አጥነትን ከመቅረፍና ፈጠራን ከማበረታት አንጻር የፕሮግረሞቹ አስፈላጊነት እሰካሁን በጥናት ሳይፈተሸና ሳይገመገም ቆይቷል ብለዋል፡፡ የኮሌጁ ዲን ቀጥለውም እንደገለጹት ከዚህ ስልጠና በኃላ ግን መስፈርቱ በሚጠይቀው መሰረት ሰነዶች ተዘጋጅተውና እያንዳንዱ ፕሮግራሞች ጥናት እና ግምገማ ተካሂዶባቸው ከሚገኙትም ውጤቶች በመነሳት የፕሮግራም ስርዓተ-ትምህርት ክለሳ፣ ቅየራ፣ በአዲስ መልክ የማዋቀር እንዲሁም አላስፈላጊ የሆኑትንም እስከመዝጋት ድረስ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስራዎች በቀጣይ ይሰራሉ ብለዋል፡፡
ዶ/ር ቸሩ አፅመጊዮርጊስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጥራት ማረጋገጫና ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ተባባሪ ዳይሬክተር ስልጠናውን በሚሰጡበት ወቅት እንደገለጹት የጥራት ኦዲት እንደሀገር በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሰፋ ያለ ጥናትና ግምገማ ተካሂዶ የጥናቱ ውጤት ለሚመለከተው አካል መላኩን ገልጸው የዚህ መሰሉ የጥራት ኦዲትን በፕሮግራም ደረጃ ማሰልጠኑ እያንዳንዳቸው ኮሌጆች ያሉዋቸውን ፕሮግራሞች እንዴት እንደሚገመግሙ፣ የኦዲት ጥቅምንና ኣላማ ተረድተው እራሳቸውን እንዲፈትሹ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ቸሩ አክለውም በሀገር አቀፍ ደረጃም በፕሮግራም መብዛት ምክንያት የምሩቃንን ቅጥር ችግሮቻችንን የሚፈታ እና አላስፈላጊ የሆኑትን ፕሮግራሞች በማስቀረት ጠቃሚ የሆኑት ላይ ለማተኮር እና ብቁ ምሩቃኖች ለማፍራት አስፈላጊ ፕሮግራሞችን ለመቅረጽ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡