የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያና የመምህር መምሪያ መጽሐፍት ረቂቅ ላይ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ አዘጋጀ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያና የመምህር መምሪያ መጽሐፍት ረቂቅ ላይ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ አዘጋጀ።

ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሌሎች የልህቀት ማዕከላት ማለትም ከአዲስ አበባ፣ ባህርዳር እና ጂማ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ከ9ኛ-12ኛ ክፍል የተማሪ መማሪያና የመምህር መምሪያ መጽሐፍት ላይ አገር አቀፍ የምክክር መድረኩን ከጥቅምት23-30/2014 ዓ.ም በቢሾፍቱ አዘጋጅቷል፡፡

ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው እንደገለጹት ከሁሉ አስቀድሜ አገራችን ከውጭና ከውስጥ የተቃጣባትን ጦርነት በመቋቋም የነገን ትውልድ ለመቅረጽ የሚያስችል ቁልፍ የአጠቃላይ ት/ት አካል በሆነው የተማሪ መማሪያና የመምህሩ መምሪያ መጽሐፍት ረቂቅ ግምገማዊ የምክክር መድረክ ላይ በመገኘታችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ እያልኩኝ በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ ከሚገኙ ኮሌጆች አንዱ የሆነው የትምህርት ኮሌጅ የዩኒቨርሲቲውን አቅም በማስተባበር በአገር አቀፍ ደረጃ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ከተመረጡት የመምህራን ት/ት እና የትምህርት አመራር ልህቀት ማዕከል እንደሀገር ተመርጦ ከ9ኛ-12ኛ ክፍል እንዲሁም በተመረጡ ከ1ኛ-8ኛ ክፍሎች የተማሪ መማሪያና የመምህሩ መምሪያ መጽሐፍት፣ እነዚህንም መጽሐፍት ለርቀት ት/ት በሚያመች ሁኔታ የተማሪ መማሪያ ማዘጋጀት እና የጎልማሶች ክህሎት ማሳደጊያ ሞጁሎች የማዘጋጀት ኃላፊነትን ከአራቱም የልህቀት ማዕከል ዩኒቨርሲቲዎች ባለሙያዎችን በመምረጥ የማስተባበር ሚናውን በተገቢው በመወጣት ስራውን እዚህ ደረጃ አድርሰናል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ቴዎድሮስ ሽዋረገጥ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዳይሬክተር በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንደገለጹት ከዚህ ቀደም የነበረው የትምህርት ስርዓት ለብዙ ዓመታት የተደራሽነት፣ የጥራት፣ የአግባብነት፣ የፍትሃዊነት እንዲሁም የብቃት ችግሮችን ሲያስተናግድ የቆየ ከመሆኑም በተጨማሪ በአዲሱ የት/ትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ በተካሄዱ ጥናቶችና ምርምሮች ስርዓተ ትምህርቱ በይዘት የታጨቀ፣ በት/ት አይነቶቹ ብዛት የተወጠረ፣ በይዘት ላይ ያተኮረ፣ ከተማሪዎችና ከማህበረሰቡ ህይወትና ኑሮ እንደዚሁም ከምርትና በተለይም ከሀገር በቀል እውቀቶች  ጋር ያልተቆራኘ፣ ተማሪዎች ተገቢውን ሞራላዊ እውቀትና ክህሎት እንዲላበሱ ያላደረገና ልዩ ፍላጎትና ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በተገቢው መንገድ ሊያስተናግድ ያልቻለ መሆኑን በማመላከቱ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ ለማስገኘት የሚያስችለው የዚህን መሰሉ እንቅስቃሴ ሊጀመር መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር ቴዎድሮስ አክለውም በዚህ የግምገማና የምክክር መድረክም የተዘጋጁትን መጽሐፍት ወደ ሙከራ ትግበራ ከመግባቱ በፊት መጽሐፍቱ የበለጠ እንዲጎለብቱ ማድረግ ሲሆን ይህንን የምናደርገውም አንደኛ እንደወላጅ ልጆቻችን የተሻለና ጥራት ያለው ት/ት እንዲያገኙ፤ እንደትምህርት ባለሙያ ተማሪዎቻችን የሚጠበቀውን ከፍተኛ የመማር ውጤት እንዲያስመዘግቡ በሚያስችል ደረጃ ያለንን አስተያየት በመስጠት መጽሐፍቱን ማዳበር ስለሚገባን ነው ብለዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አብርሃም ቱሉ እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ልህቀት ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተከተል አዳነ በበኩላቸው የረቂቅ መጽሐፍቶቹ ዝግጅት ምን እንደሚመስል፣ የነበሩ ተግዳሮቶችና በቀጣዮቹ ቀናቶች ስለሚደረጉት የመጽሐፍቶቹ ግምገማ በዝርዝር አስረድተው በዚህ ዝግጅት ላይ አሻራቸውን ላሳረፉ ምሁራን ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በቀጣዮቹ ቀናትም በ72 የትምህርት አይነት በተዘጋጁት የተማሪ መማሪያና የመምህር መምሪያ መጽሐፍት ረቂቅ ላይ ግምገማና ውይይት እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et