የግብርና ኮሌጅ የስነምግባር መከታተያና የፀረሙስና ቡድን ለኮሌጁ የስራ ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ

የግብርና ኮሌጅ የስነምግባር መከታተያና የፀረሙስና ቡድን ለኮሌጁ የስራ ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ።

ከጥቅምት 18-19/ 2014 ዓ.ም ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የአካዳሚክና አስተዳደር ስራ ክፍል ኃላፊዎች በወንዶ ገነት ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ሲዳ አዳራሽ በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ የኮሌጁ አካዳሚክ ጉዳዮች ተባባሪ ዲን ዶ/ር ዘሪሁን ደምረው በቦታው ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም የስነ-ምግባርና የሙስና ችግሮች በሀገር እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩና ዘርፈ ብዙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሆነው መቆየታቸውን አንስተው፤ በቅርብ ጊዜያት የነበረውን የሀገራችንን ሁኔታ ብንመለከት እንኳን ላለፉት 27 ዓመታት በግንባታ፣ በመሰረተ ልማት፣ በግዢ እና በሌሎች ዘርፎች ይታዩ የነበሩ የሙስና ችግሮች እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ እንዳስከፈሉን ገልፀዋል።

ተባባሪ ዲኑ አክለውም ሙስና እንደ አሁኑ ጊዜ የኢኮኖሚውና የፖለቲካ ችግር ከመሆኑ በፊት በተለምዶ እጅ መንሻ ወይም ጉቦ ይባል እንደነበርና ይህም ድርጊት አድጎ ደንበኛን በስርአቱ አለማስተናገድ፣ የመንግስት የስራ ስአትን አለማክበር፣ በግዢና በቅጥር ዙሪያ አላስፈላጊ ምክንያቶችን በመደርደር የግለሰቦችን ህይወት ከመጉዳት አልፎ ሀገር እስከማፍረስ አድጎ አሁን ሀገራችን ለምትገኝበት ሁኔታ ትልቅ ድርሻ መወጣቱን ተናግረዋል። የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር በዩኒቨርስቲው ውስጥ ሲስፋፋ በጣም አስከፊ ገፅታ እንደሚኖረው ጠቁመው ኮሌጁ የመማር ማስተማርና የምርምር ስራ የሚካሄድበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተማሪዎቻችን ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የመጡ በመሆናቸው  ከሚማሩት መደበኛ ትምህርት ሌላ በግቢያችን የመልካም አስተዳደር ቾግሮች ቢታዩ የተሻለ ዜጋ ከመፍጠር ይልቅ የስነ-ምግባር ችግሮችን ማስተዋወቁ ይጎላል ይህም ወደ መጡበት አካባቢ ለሚመለሱት ተማሪዎቻችን ከባድ ፈተናን ይደቅንባቸዋል ብለዋል።

ተባባሪ ዲኑ በንግግራቸው መጨረሻም ሁሉም የኮሌጃችን የአዳሚክና አስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም የስራ ክፍል ኃላፊዎች የላቀ የስራ አፈፃፀም ማስመዝገብ ይቻል ዘንድ የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመከላከል የወጡ አዋጆችን ደንቦችንና መመሪያዎችን ማወቅና መተግበር እንደሚጠበቅባቸው አበክረው ተናግረዋል ።

የኮሌጁ የስነ-ምግባር መከላከያና የፀረ ሙስና ቡድን ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ሳህሉ በበኩላቸው የዛሬው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሁለት ዋና ዋና አላማዋች እንዳሉት የገለጹ ሲሆን የመጀመሪያውም ይህ ክፍል በኮሌጅ ደረጃ አዲስ የተቋቋመ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ ዋናው ስራ ውስጥ ከመግባታቸን በፊት ትውውቅ የማድረግያ መንገድ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የኮሌጁ ማህበረሰብ የስነ-ምግባር ህጎችን ደንቦችንና መመሪያዎችን አውቆ ራሱን ከመልካም አስተዳደር ችግሮች መከላከል እንዲችል ነው ብለዋል። የዛሬው ስልጠና ተሳታፊዎች በኮሌጁ በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎች ቢሆኑም በቀጣይ ለሁሉም የአካዳሚክና አስተዳደር ሰራተኛ ስልጠናው እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በመጨረሻም የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሪክተር የሆኑትና የዕለቱን ስልጠና የሰጡት  አቶ ከበደ ኩማ ሲናገሩ በስልጠናው የተሳተፉ የግብርና ኮሌጅ የስራ ክፍል ኃላፊዎች ከስልጠናው የሚያገኙአቸውን ክህሎቶች በአግባቡ በመጠቀም በመልካም አስተዳደርና ስነ-ምግባር እንዲሁም በአንዳንድ የስራ ክፍሎች አካባቢ  የሚታዩ የሙስናዎች ድርጊቶችን በማስወገድ የተሻለ ውጤታማነትን ሊያመጡ እንደሚገባ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et