ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሙጃሌ በሽታ ተጠቂ ለነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ባደረገላቸው ህክምና የመጡ ለውጦችን ለመገምገም ጉብኝት አካሄደ

ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሲዳማ ክልል ወንሾ ወረዳ ስር በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ጉብኝት አካሂዷል፡፡

ባካሄደው በዚሁ ጉብኝት ላይ በቦታው የተገኙት የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የላብራቶሪ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር ሰለሞን አስናቀ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎቱ ስር ቀደም ሲል ባካሄደው ጥናት መሰረት የሙጀሌ በሽታ ትኩረት የተነፈገው ነገር ግን በበሽታው ተጠቂ ለሆኑት በርካታ ማህበራዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ጫናዎችን የሚያሳድር ሆኖ መገኘቱን አስታውሰዋል። አክለውም ዩኒቨርሲቲው ምርምር ማድረግ ብቻ ላይ ሳይወሰን መፍትሄ ለማፈላለግም በሰራው ስራ መሰረት በጉዳዩ ዙሪያ የበርካታ ሀገራትን ልምድ በመቀመር በመጨረሻም የተቀናጀ ስራ መሰራት እንዳለበት በመታመኑ በወረዳው ለሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተከታታይ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመተባበርም በወረዳው ስር በሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች ለሚገኙ የበሽታው ተጠቂ የማህበረሰብ ክፍሎች ህክምና መሰጠቱን አስረድተዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ መኮንን ግርማ በበኩላቸው ህክምናው የተሰጠው የመታጠቢያ ኬሚካሎችን፣ ሳሙናዎችን እና የቫዝሊን ቅባት በመጠቀም መሆኑን ገልፀው በዚህም የተነሳ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ከቁስሉ እና ከሚያስከትለው ከፍተኛ ህመም የተነሳ መንቀሳቀስ የማይችሉ የነበሩ ታማሚዎች በአሁኑ ወቅት የተሰጣቸውን ህክምና ተከትሎ መራመድ እንዲሁም የቀደመ ስራቸውን በማካሄድ ለቤተሰቦቻቸው ሸክም ከመሆን መላቀቃቸውን፣ እንዲሁም ከዚሁ በሽታ ጋር በተያያዘ ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው ማየት ችለናል ብለዋል። አቶ መኮንን አክለውም ታካሚዎች ህክምናውን ካጠናቀቁ በኃላ ተመልሰው ለበሽታው ተጋላጭ እንዳይሆኑ በሽታውን እንዴት መከላከል እንዳለባቸው ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

በወንሾ ወረዳ መናፈሻ ቀበሌ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ ወ/ሮ ወይንሼት አማንቴ ዩኒቨርሲቲው ለሰጣቸው ስልጠና ምስጋናቸውን አቅርበው በተካሄደው የሙጀሌ ህክምና በቀበሌያቸው ተጨባጭ የጤና መሻሻል መገኘቱን ተናግረዋል። በሽታው ንፅህናን በመጠበቅ ሊቀረፍ የሚችል እንደመሆኑ ሌሎች ከንጽህና ጉድለት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመቀነስም ማስቻሉን ገልጸዋል። የበሽታው ተጠቂዎች ድጋሚ በበሽታው እንዳይጠቁ እንዲሁም በሽታው የሌለባቸው ደግሞ እራሳቸውን ከበሽታው ለመከላከል ቤታቸውን በእበት በመለቅለቅ የትንኟን መራባት ለመቆጣጠር የሚያስችል ስልጠና መሰጠቱን አብራርተዋል።

በመጨረሻም የበሽታው ተጠቂ ከነበሩና ህክምና ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል የሆኑት በወንሾ ወረዳ የመናፈሻ ቀበሌ ነዋሪዎቹ ወ/ሮ ማርታ አብርሃም፣ አቶ ሸንኮራ ወናጎ እና አቶ ሂሮ ቃርፋፋ እንደገለጹት በሽታው በብዙ መልኩ በህይወታቸው ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን እና አሁን በተደረገላቸው ህክምና ግን በጤንነታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ማየት መቻላቸውን ገልጸዋል። መልእክታቸውን ሲያስተላልፉም እንደ እነርሱ የበሽታው ተጠቂ ሆነው ነገር ግን በተለያየ ምክንያት በቤታቸው ያሉ ሁሉ ምንም ሳይፈሩ ህክምናውን እንዲወስዱ እና ከበሽታው እንዲድኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et