የሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶች እና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የተካሄደውን ይህን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ዳይሬክቶሬቱ ከአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን ስልጠናውም በስርዓተ ፆታ፣ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ የሴቶች መብት፣ የስነተዋልዶ ጤናና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ የተሰጠ ነበር።

በስልጠናው ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መሳይ ሀይሉ እንደገለጹት በሀገራችን ኢትዮጵያ በስነተዋልዶና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዙሪያ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸው ይህም በመሆኑ በርካታ ማህበራዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ጉዳቶች መከሰታቸውን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው የችግሩን ስፋትና የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት ለተማሪዎች እንዲሁም ለአስተዳደር ሰራተኞች በችግሮቹ ዙሪያ ግንዛቤን ከመፍጠር አንስቶ ምቹ የመማሪያና የስራ ከባቢን ምቹ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አክለውም ይህ ስራ በአንድ የስራ ክፍል ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያገባኛል በሚል ስሜት መንቀሳቀስ እንዳለበት አስገንዝበዋል። ይህ ስልጠናም ግንዛቤን ከመፍጠር በተጨማሪ በሚቀርቡ ሰነዶች ላይ በመወያየትና ሀሳቦችን በማንሸራሸር ውጤታማ ግብዓቶች የሚሰበሰቡበት እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶች እና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር ወ/ሮ ምህረት ገነነ በበኩላቸው ዳይሬክቶሬቱ በተለያዩ ጊዜያት ለተማሪዎች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች መሰል ስልጠናዎችን መስጠቱን አስታውሰው በዚህም የተነሳ መልካም ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። ይህ ስልጠና በአስተዳደር ዘርፉ ላይ ያሉትን ሰራተኞች ለማብቃት እና ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው የስልጠናው ተካፋዮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከተማሪዎች ጋር ግንኙነት ስላላቸው ዛሬ የሚያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ተማሪዎችንም ለማብቃት በሚሰራው ስራ ላይ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ መምህርት የሆኑት እና በዕለቱ ስልጠናውን ከሰጡ ባለሙያዎች መካከል አንዷ የነበሩት ወ/ሮ ቤተልሔም መታፈሪያ ጾታ ተፈጥሯዊ እና የማይለወጥ መሆኑን ነገር ግን ስርዓተ ጾታ እንደ ማህበረሰቡ የእድገት ደረጃ የሚለዋወጥ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡ በየወቅቱ የሚካሄዱ ምርምሮችና በስልጠናዎች ወቅት የሚነሱ ሀሳቦች የስርዓተ ትምህርቱ አካል ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። ይህም ለውጥ ሊመጣ የሚችለው የማህበረሰቡን አመለካከቶች ሊቀርጹ ከሚችሉ ተቋማት መካከል ከሆኑት ከዩኒቨርሲቲዎች በመሆኑ በየወቅቱ የሚካሄዱ ምርምሮችና በስልጠናዎች ወቅት የሚነሱ ሀሳቦች የስርዓተ ትምህርቱ አካል ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም ወ/ሮ ቤተልሔም የስልጠናው ዓላማዎች ከሆኑት መካከል አንዱ በስርዓተ ጾታ ዙሪያ ስላሉ ህጎች ግንዛቤን መፍጠር በመሆኑ በህገ መንግስቱ እንዲሁም በሌሎች ህጎች ላይ ተደንግገው ስለሚገኙ እኚሁ ህጎች በቂ ዕውቀት ሊኖረን ስለሚገባ ስልጠናው በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ብቻ ሳይገደብ ችግሩ በስፋት በሚስተዋልባቸው የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎችም ሊዳረስ እንደሚገባ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et