የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በወንዶ ገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ በመገኘት 3ኛውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ሰኔ10 ቀን 2013 ዓ.ም አካሂዷል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በመርሃ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት በሀገራችን በዚህ ዓመት 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ለ3ኛ ጊዜ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በተለያዩ ቦታዎች ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን ዩኒቨርሲቲያችንም ከዚህ ቀደም በዋናው ግቢ እና በሲዳማ ክልል ቦርቻ ወረዳ የችግኝ ተከላ መከናወኑን አስታውሰው የዛሬውም ለ3ኛ ጊዜ የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራኖች እና የአስተዳደር ሰራተኞችን በማሳተፍ በወንዶ ገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ 8200 ችግኞችን ተክለናል ብለዋል፡፡
ደንን ማጥፋት ራስን፣ ሰዎችን ማጥፋት ነው ያሉት ዶ/ር አያኖ አክለውም በዓለማችን ብሎም በሀገራችን የአየር ንብረት ለውጥ መንስዔዎች ውስጥ አንዱ የደኖች መመናመን በመሆኑ ችግኞችን በመትከል፣ በመንከባከብና ልዩ ትኩረት ሰጥተን በማሳደግ ተፈጥሮን በተፈጥሮ ማከም ዘላቂና ውጤታማ አካሄድ ሲሆን የዕለቱን መርሃ-ግብር እንዲሳካ ላደረጉት ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴ/ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፣ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት እና ለወንዶ ገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሞቱማ ቶሌራ የወንዶ ገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ኮሌጁ ላላፉት 43 ዓመታት በደን ላይ የረጅም ጊዜ ምርምርና ልምድ ያካበተ በመሆኑ እንደሀገር የተያዘውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ለመደገፍ ከ180000 በላይ ችግኞችን አዘጋጅቶ ለዩኒቨርሲቲው፣ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለተለያዩ ድርጅቶች ለሚፈልጉት ዓላማ እያሰራጨንና እያማከርን ሲሆን በዛሬውም መርሃ-ግብር በሌሎች ቦታዎች እየጠፉ የሚገኙ ብርቅዬ የሀበሻ ጽድ ችግኞችን ዝርያቸውን ለማቆየትና ለማብዛት ተክለናል በማለት ገልጸዋል፡፡