ኮሌጁ በደን አያያዝ፣ በደን ስነ-ምህዳር ጥናትና ሲልቪካልቸር እና በዱር ህይወት ስነ-ምህዳር ዙሪያ የ3ኛ ድግሪ ፕሮግራሞችን ለመክፈት በ14/09/2013 ዓ.ም ውጫዊ ግምገማ አስደርጓል፡፡
የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሞቱማ ቶሌራ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት ኮሌጁ ከአርባ ዓመት በላይ በደንና ተፈጥሮ ሃብት ዙሪያ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ በርካታ ስራዎችን በመስራቱ እንደ ሃገር በዘርፉ የልዕቀት ማዕከል መሆኑን ገልጸው ሃገራችን የአረንጓዴ ልማት አሻራ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች በመሆኑ ይሄንንም በእውቀትና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመምራትና ለማስቀጠል የተማረ ኃይል ስለሚያስፈልግ እነዚህን ፕሮግራሞች መክፈቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሞቱማ አክለውም ፕሮግራሞቹን ለመክፈት ከዚህ በፊት አስፈላጊው የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ በዚሁ ዘርፍ በሃገራችን መዋቅሩ እየተሰራ በመሆኑ በቂ የተማረ ኃይል ለማፍራት የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ሰነዶች ተዘጋጅተው የውስጥ ግምገማ የተካሄደባቸው ሲሆን ከዛሬውም ግምገማ ግብዓቶችን ወስደን ለዩኒቨርሲቲው በማቅረብ ሲጸድቅ ተማሪዎችን ተቀብለን እናስተምራለን ብለዋል፡፡
ዶ/ር መሰለ ነጋሽ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንደገለጹት ፕሮግራሞቹ ሃገሪቱ ከያዘቸው አቅጣጫ ጋር የሚያያዙ በመሆኑ እንዲሁም ደንን በዘላቂ ሁኔታ ለመጠቀም፣ ያለንን የደን ሀብታችንንና በውስጡ የሚገኙትን የዱር እንሰሳዎችን ለማወቅ እና የደንን መመናመንን እና ውድመትን ለመታደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለመስራት በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ጠቃሚ መሆኑን ተናግረው የሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎች ምርምር ላይ ስለሚያተኩሩ ችግሮችን በመለየት ወደ መፍትሄዎቻቸው ለመምጣት እና ለፖሊሲ አዘጋጆች ትልቅ ግብዓት ከመፍጠሩም በተጨማሪ የአረንጓዴ አሻራን ለማስቀጠል ለሀገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡
በዕለቱም የቀረቡት የትምህርት ሰነዶች በምሁራኖች በሰፊው ተገምግመውና ገንቢ አስተያየቶች ተሰጥቶባቸው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡