ግንቦት 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ 2ኛውን ሀገር አቀፋዊ የሳይንስ ኮንፍረንስ አካሂዷል፡፡
በተካሄደው በዚሁ ኮንፈረንስ ላይ ተጋባዥ ጥናት አቅራቢዎች፣ ከደ/ብ/ብ/ክ እና ሲዳማ ክልሎች የተውጣጡ ተወካዮች፣ በርካታ ተመራማሪዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ሆነዋል።
የተፈጥሮ እና ኮምፒቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዘይቱ ጋሻው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ባደረጉበት ወቅት "ሳይንሳዊ ምርምር ለዘላቂ ዕድገት፣ አረንጓዴ ቴክኖሎጂ እና የዳታ አብዮት" በሚል ጭብጥ እየተካሄደ ያለውን ኮንፈረንስ አስፈላጊነት ሲገልጹ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ህዝቦቻቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ያለ የምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች እጥረት እየገጠማቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል። አካባቢያችንን መጠበቅ የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ እንድንጠቀም እንደሚያስችል ቢታመንም የሰው ልጆች ግን ይህን ሲያደርጉ አይታይም። አካባቢ እና የተፈጥሮ ሀብት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በእጅጉ አስፈላጊዎች መሆናቸው በመገንዘብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተሰሩ በርካታ ስራዎች የምግብ ምርትን በብዙ እጥፍ ማሳደግ መቻሉን ገልጸው ለዚህም መሳካት የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ አዳዲስ ዝርያዎች፣ የመንግስት ፖሊሲ ማሻሻያዎች እና ተጨማሪ በጀት መመደቡን እንደ ምክንያትነት አቅርበዋል።
ዲኑ ንግግራቸውን ሲቀጥሉም ይሁን እንጂ የዚህ ስኬት ዘላቂነት ላይ ብዙ ጥያቄዎች እንደሚነሱና በዋናነትም መግታት ያልተቻለው በአካባቢ እና የተፈጥሮ ሀብት ላይ የተደቀነው ሰው ሰራሽ አደጋ ለዚሁ ተጠቃሽ ነው ብለዋል። ሀገራችን ኢትዮጺያ የበርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ በመጣው መሬትን ለግጦሽ እና ለመኖርያነት ማዋል በርካታ ዛፎች እየወደሙ እንዳሉና በዚህም የተነሳ የአየር ንብረት ለውጥ እየተከሰተ እንደሚገኝ በተጨማሪም በርካታ የውሃ ምንጮቻችን የመድረቅ እና በውስጣቸው ያሉ የእንስሳት ሀብት የመመናመን አደጋ ተደቅኖባቸዋል ብለዋል። በእነኚህ ሁለት ቀናት በሚካሄደው ኮንፍረንስ በዘርፉ የተካሄዱ በርካታ ምርምሮች እንደሚቀርቡበትና ከእነዚህም መነሻነት እንደ ሀገር እንዴት መጓዝ እንዳለብን የመፍትሄ ሀሳቦች የሚፈልቁበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ ባራሶ በበኩላቸው አካባቢ እና የምግብ ዋስትና ለዘላቂ ልማት ዋነኞቹ ምሶሶዎች መሆናቸውን ጠቅሰው እ.ኤ.አ በ2020 በዓለም አቀፉ የምግብ ዋስትና ግምገማ ሪፖርት መሰረት መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው 76 ሀገራት የምግብ ዋስትናን ያላረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 844 ሚሊየን መሆኑ ሲጠቀስ በሀገራችን ኢትዮጲያም 20 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የምግብ ዋስትናውን እንዳላረጋገጠ መጠቀሱን አንሰተው ይህ እንደኛ አብዛኛው ህዝብ አርሶአደር በሆነበት ሀገር የችግሩን አሳሳቢነት ከፍተኛ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። መንግስት በተለያዩ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ ቢሆንም እንደዛሬ ባሉ ኮንፍረንሶች ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች የሚያቀርቧቸው የምርምር ፕሮጀክቶች እና የትግበራ እቅዶች አይተኬ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
ከምርምር ጥናት አቅራቢዎች መካከል አንዱ የሆኑት በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ጂኦ ፊዚክስ፣ ህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም ዳይሬክተሩ ፕ/ር አታላይ አየለ ጥናታቸውን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ ምርምሮችን ማካሄድ እና ግኝቶችን በጋራ መገምገም እንደሚገባ አስረድተዋል። ኢትዮጲያ በርካታ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶች ቢኖሯትም ለሌሎች እንጂ ለእራሷ እምብዛም ስትጠቀምባቸው አይስተዋልም ያሉት ፕሮፌሰሩ ይልቁንም አብዛኛውን ጊዜ የእኛን ለም አፈር ይዞ በመሄድ ለጎርፍ እና ረሃብ ተጋላጭ አድርጓት ቆይቷል ብለዋል።በርካታ ፕሮጀክቶች ያለ በቂ ጥናት እና ምርምር ተጀምረው የታሰበላቸውን ግብ ሳያሳኩ መቅረታቸውን አውስተው እንዲህ አይነቱ የምርምር ኮንፈረንስ ሲዘጋጅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በያገባኛል ስሜት ተቀራርበው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም ለሁለቱ ቀናት በቆየው ኮንፍረንስ ላይ በርካታ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ስለ ታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ የፕሮጀክት ምርምር ሂደቶች እና በኢትዮጲያ ስምጥ ሸለቆ ላይ ስላለው የእሳተ ገሞራ ስጋት የቀረቡት ጥናቶች ይጠቀሳሉ። በዕለቱም በነበረው ውይይት በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተሰንዝረው መልስ ተሰጥቶባቸዋል።