የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጆርናል ስርዓት መተግበሪያ ሶፍትዌር ይፋ አደረገ

ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕ/ጽ/ቤት በአይ.ሲ.ቲ ዳይሬክቶሬት በኩል ጆርናሎች የሚውል አዲስ የኦንላየን መተግበሪያ ሶፍትዌር ይፋ አድርጓል፡፡

ሶፍትዌሩ ከዚህ ቀደም ለነበሩት ሁለት ጆርናሎች እና አዳዲስ ለሚመሰረቱት ስምንት ጆርናሎች የሚውል መሆኑም ተገልጾአል፡፡

የአይ. ኤስ.ቲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ገ/ማርያም እንደገለጹት ይሄንን መተግበሪያ እንድንሰራ  በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕ/ጽ/ቤት በኩል ጥያቄ ከቀረበልን ሰዓት ጀምሮ ባለሙያዎችን በማቀናጀት የዓለም አቀፍ ጆርናል መተግበሪያ ምን እንደሚመስልና ምን ማሟላት እንዳለበት በመምከር ይሄንን መተግበሪያ ያዘጋጀን ሲሆን መተግበሪያው ለዩኒቨርሲቲያችን በሚመች መልኩ የተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ረጅም የሚባል ልምድ ያለው ሲሆን በእነዚህ ዓመታትም በርካታ ምርምሮችን እያደረገ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ ቢሆንም የጆርናሎቹ መጠን ሁለት ብቻ በመሆናቸው ለዩኒቨርሲቲው በቂ ስላልሆኑ እና በኢትዮጵያ ውስጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው ከተመረጡት አንዱ በመሆኑ ምርምሮች ላይ ትኩረት ሰጥተን ለምንሰራቸው ስራዎች እንዲረዳን የምርምር ጆርናሎችን መጨመር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ስምንት ተጨማሪ የምርምር ጆርናሎች ተመስርተዋል ብለዋል፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም እነዚህ የምርምር ጆርናሎችም ተደራሽ እንዲሆኑና ተመራማሪዎችም የሰሯቸውን የምርምር ውጤቶች አሳትመው እንዲያሰራጩ አሁን ባለንበት ዘመን ጊዜው የሚፈልገውን ኦንላየን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተዘጋጁትን መተግበሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ቀጣይነትና ጥራት እንዲኖራቸው በርትተን መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በዕለቱ የማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ከዚህ በፊት የአይ.ሲ.ቲ ዳይሬክቶሬት ሰርቶ ተግባራዊ ስላደረጋቸው የተለያዩ ችግር ፈቺ መተግበሪያዎች እና ስለ አዲሱ የኦንላየን ጆርናል ስርዓት መተግበሪያው ዙሪያ በባለሞያዎች ገለጻ ከተደረገ በኃላ በቀረበው የሶፍትዌር መተግበሪያ ላይ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም በስራው ላይ ለተሳተፉ ባለሞያዎች የምስክር ወረቀት በመስጠት የእለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et