ግብርና ኮሌጅ በከብቶች ላይ እየሠራ በሚገኘው ምርምር ዙሪያ ገለጻ እና የመስክ ጉብኝት አካሄደ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ የእንስሳት አያያዝና የከብት ግጦሽ ተመራማሪዎች ሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በምርምራቸው ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በገለጻው ላይ ከደብብ እና ሲዳማ ክልሎች እንዲሁም ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ ባራሶ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። በሰባት ካምፖሶች ተደራጅቶ ከ40,000 በላይ ተማሪዎችን በ103 የመጀመሪያ ድግሪ፣ በ124 የሁለተኛ ድግሪ እንዲሁም በ35 የፒ.ኤች.ዲ የትምህርት ፕሮግራሞች እያስተማረ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው  ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ ጋር በመሆን ከ62 በላይ የሆኑ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም የLovestock system innovation Lab (LSIL) በዩኒቨርሲቲው እየተካሄዱ ካሉ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑንና ዋነኛ ትኩረቱንም በእንሰሳት መኖና ስነ-ምግብ፣ በወተት እና የወተት ከብቶች አያያዝ፣ የከብቶች ስጋና ስነ-ምግብ እንዲሁም የምግብ ደህንነት ላይ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በ2017 በበርካታ ተቋማት የጋራ ትብብር ተቀርጾ የተጀመረና አሜሪካን ሀገር በሚገኘው university of Florida የሚተዳደር ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ መጠናቀቁ የደረሰ ፕሮጀክት ነው ብለው ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም ለፕሮጀክቱ መሳካት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለሰሩ ተቋማት እና ግለሰቦች ምስጋናን አቅርበዋል።

የእንስሳት ሳይንስ ትምሀርት ክፍል ሀላፊና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ስንታየው ይግረም በበኩላቸው አገራችን ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሀብቷ የታወቀች ብትሆንም በእንስሳት አያያዝና የመኖ አቅርቦት ዙሪያ በሚስተዋሉ ችግሮች የተነሳ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን ተናግረዋል። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በLSIL ፕሮጀክት ባገኙት ድጋፍ ታግዘው ችግር ፈቺ ምርምር ሲያካሂዱ የቆዩ ሲሆን በዛሬው ውይይትም ስለደረሱበት ውጤት ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የመስክ ጉብኝት ያደርጋሉ ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ተመራማሪዎች የሚገኟቸውን አዳዲስ ግኝቶች ከአምራቹ ማህበረሰብ ጋር ለማገናኘት እንዲያስችለው በዘርፍ የተማሩ ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ 7 ተጨማሪ የፒ.ኤ.ች.ዲ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የLSIL ፕሮጀክት አስተባባሪና ተመራማሪ ፕ/ር አዱኛ ቶሌራ ከመስክ ጉብኝቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ምርምሩ የተጀመረው  በውጭ ሀገር  ዲቃላ ከብት ላይ ቢሆንም ለወደፊት በሀገር  በቀል ከብቶች ላይ  እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ፕሮፌሰሩ አክለውም የእንስሳት ወተት የህፃናት መቀንጨር ችግርን ለመፍታትና የአይምሮ እድገታቸውና የማሰብ ችሎታቸው ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው በእንስሳት መኖ አቅርቦት ማነስ ምክንያት በዘርፉ ላይ የሚታዪ ማነቆዎችን ለመቀነስ የመንግሰት የፖሊሲ ለውጥ፣ የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎና በሙያው የሰለጠኑ ምሁራን በእንስሳት ጤና ላይ የየበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም  የሀዋሳ ዪኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዋች በተመራማሪዎቹ መልስ እና ማብራሪያ እንዲሰጥ መድረኩን የመሩ ሲሆን በእንስሳት ተዋፅኦ ምርት መቀነስና የመኖ እጥረት ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል በዚህ ገለጻና ውይይት ላይ የተነሱ መፍትሄዎች አይነተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል  የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et