የሳይንስና ቴክኖሎጂ እና ምንድስና ማዕከል በሮቦቲክስ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

ሚያዚያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲው የሳይንስ ማዕከል በተካሄደው የምረቃ ሥነ-ስርዓት ስልጠናውን የወሰዱ 24 ተማሪዎች የተመረቁ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 7 ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የማዕከሉ ኃላፊ ዶ/ር ምስራቅ ጌታሁን እንደገለጹት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምህንድስና ማዕከል ወይም STEM center በሚስተር ገልፋንድ ድጋፍና መስራችነት በ2007 ዓ.ም እንደተመሰረተና ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሳይንስ፣ ሂሳብ፣ ሮቦቲክስና ኤሌክትሮኒክስ የትምህርት ዘርፎች የአንደኛ መለስተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እና መምህራንን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት አስራ ሁለት ከ7-8 ክፍል የተወጣጡ እንዲሁም ስድሳ ከ9-10 ክፍል የተወጣጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ዶ/ር መብርሃቱ ሙላቱ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቶች ትስስር ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ከሚገኙ ስምንቱ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች አንዱ እንደመሆኑ በዚህ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የSTEM ማዕከሉን በተለያዩ መስኮች በማገዝ ብቁና ፈጣሪ ታዳጊዎችን ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የSTEM power የሀገር ውስጥና የምስራቅ አፍሪካ ተጠሪ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ወ/ሪት ቅድስት ገብረ አምላክ በበኩላቸው ማዕከሉ ከተመሰረተ አስራ አንድ አመት ማስቆጠሩን ጠቅሰው አርባ ስምንት ከሚጠጉት ማዕከላት መካከልም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ማዕከል እጅግ ውጤታማ ከሆኑት ማዕከላት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ዛሬ በዚህ የምረቃ ስርዓት ላይ በመገኘታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ኃላፊዋ በመቀጠልም ማዕከሉን ተዘዋውረው እንደሚጎበኙና ከዩኒቨርሲቲው ጋር በበለጠ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም መሆኑን ተናግረዋል።

በመጨረሻም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ሲናገሩ ማዕከሉ መጀመሪያ በተቋቋመበት ወቅት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዘንድ ሙሉ ግንዛቤ ያልነበረ መሆኑን አውስተው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ዘርፉ የመንግስት ትኩረት እየሆነ የመጣ መሆኑንና ዩኒቨርሲቲውም ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጠው ገልጸዋል። ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነትም ዩኒቨርሲቲው ከማዕከሉ ጋር የበለጠ እንዲሰራና ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያደርገው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et