የማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዓመታዊውን የምርምር ግምገማ አካሄደ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ከመጋቢት 23-24/2013 ዓ.ም ዓመታዊውን የምርምር ግምገማ ባካሄደበት ወቅት የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዳኜ ሽብሩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ይህ  አራተኛው አመታዊ ግምገማ መሆኑን ገልጸዋል።

ትምህርት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታየውን ድህነት በመቀነስ እና እድገትን በማምጣት ረገድ አይነተኛ ሚና ስለሚጫወት መንግስት ለዚህ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን አንስተው በዚህም ረገድ የሚጠበቅበትን ድርሻ ለመወጣት ሶሰት ኢንሰቲትዩቶች፣ ስምንት ኮሌጆችና ከመቶ የሚበልጡ ዲፖርትመንቶች ያሉት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቁርጠኝነት እየሰራ እንዳለ ተናግረዋል። ቀደም ብለው ከተመሰረቱ ኮሌጆች አንዱ የሆነው የማህበረሰብ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በውስጡ ከአራት ሺህ በላይ በቀን፣ በማታ፣ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናትና በክረምት መርሐ ግብር የሚማሩ ተማሪዎች፤ ከሁለት መቶ በላይ የአካዳሚክ እንዲሁም ከሀያ አምስት በላይ የአስተዳደር ሰራተኞች ያሉት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ስምንት የመጀመርያ ዲግሪ፣ ሰባት የሁለተኛ ዲግሪ እና ሁለት የፒኤችዲ ፕሮግራሞችን እየሰጠ እንዳለ ገልጸዋል።

አክለውም ዩኒቨርሲቲዎች ከማስተማሩ በተጨማሪ በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ መሳተፍ ሀላፊነታቸው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በዚሁ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ለአብነትም በአሁኑ ሰዓት ከመንግስትና ሌሎች ተባባሪ አካላት በተገኘ የገንዘብ እርዳታ በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን በዚሁ ዘርፍ የሚሳተፉ ተመራማሪዎች ቁጥርም በየዓመቱ እየጨመረ ነው ብለዋል። በማህበረሰብ አገልግሎቱም ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ከሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ለዚህም ስራ እንዲረዳው በሀዋሳ ዙሪያ ስድስት የቴክኖሎጂ ወረዳዎችን የመረጠ ሲሆን እነዚህም ሁላ፣ ዳሌ፣ ወንዶ ገነት፣ ቦሪቻ፣ ሀዋሳ ዙሪያ እና የሀዋሳ ከተማ ወረዳዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ብቻ ሳይገደብ ከተመረጡት ወረዳዎች ባሻገርም የምርምር ስራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል። ሲያጠቃልሉም ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ግምገማ አስራ አምስት የምርምር ወረቀቶች እንደሚቀርቡ እና ተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ግምገማውን ውጤታማ እንደሚያደርጉት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል ።

የማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን የሆኑት  ዶ/ር መለሰ ማዳ በበኩላቸው የዛሬው ግምገማ በየአመቱ በኮሌጁ በተለያዩ ዲሲፕሊኖች የሚካሄደው ግምገማ አካል መሆኑን ገልጸው በዚህ ግምገማ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል። የምርምር ስራዎቹ የማህበረሰቡን ችግር ፈቺነታቸው እንደሚገመገም እና የምርምሮቹ ግኝቶች በዩኒቨርሲቲው መጽሔት እና በሶሻል ሚዲያዎች ለኮሌጁ ማህበረሰብ ተደራሽ እንደሚሆን እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃም ለማሳተም ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል። በመጨረሻም በኮሌጁ እየተከናወኑ ያሉ የምርምር ስራዎችን ለማጠናቀቅ እና አዳዲስ ምርምሮችን ለማስጀመር የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

                                                                                                      

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et