የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ የዓለም የሴቶች ቀንን አከበረ

ረዕቡ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም "የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበረሰብ እንገንባ" በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተከበረው በዚሁ በዓል ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሀ

ጌታቸው በመክፈቻ ንግግራቸው የበዓሉን ታዳሚዎች በዓለም ለ111ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ45 ጊዜ ለሚከበረው የአለም የሴቶች ቀን (March 8) እንኳን አደረሳችሁ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን በመቀጠልም ከሀገራችንን ሕዝቦች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ቢሆኑም በቁጥራቸውና በሚገባቸው ልክ በሀገሪቱ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እምብዛም መሆኑን አንስተው ነገር ግን ይህ አካሄድ የማያዋጣ በመሆኑ እንደ ሀገር ሴቶችን ወደ ፊት ለማምጣት መንግስት በትኩረት እየሰራ ሲሆን ዩኒቨርሲቲውም በበኩሉ የሴት መምህራንን  ቁጥር ለማሳደግ በመጀመርያ ድግሪ የሚመረቁና ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ለመቅጠር መወሰኑን አንስተዋል። በንግግራቸው ማጠቃለያም ሴቶች ብልህና ለሀቅ የሚወግኑ በመሆናቸው የስልጣን ቦታዎችን ቢይዙ አሁን በዓለማችን ላይ የበዛው ጦርነት፣ መፈናቀልና ሙስና በእጅጉ ይቀንሳል ብለው እንደሚያስቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል ።

የዩኒቨርሲቲው የሴቶች ህፃናት ወጣቶችና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ምህረት ገነነ ባቀረቡት ጽሁፍ የበዓሉን አጀማመር ሲያስታውሱ በወቅቱ የነበሩ ሴቶች ይደርስባቸው የነበረውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ፆታዊ እና ሁሉን አቀፍ ተጽዕኖ ለማስወገድ አስበው እንደነበር ገልጸዋል። በዓሉም ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካን ሀገር ከዛሬ መቶ አስራ አንድ አመት በፊት እ.ኤ.አ በ1909 የተከበረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተደረጉ ሰፋፊ ትግሎች በአለምአቀፍ እንዲሁም በሀገራችን ደረጃ በረካታ ለውጦች መመዝገባቸውን እንስተው ነገር ግን ገና ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ ሀሳባቸውን ገልጸዋል። ሲያጠቃልሉም ሴቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በፖለቲካው ዘርፍ እንደ ወንዶች ሁሉ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያለ ሴቶች የነቃ ተሳትፎ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ተገንዝበው ሙሉ ድጋፋቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመጨረሻም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች ሽልማት የተበረከተ ሲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሴት መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞችም እውቅና ተሰጥቷል። ሽልማቱን ያበረከቱት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሳይ ሐይሉ በግቢው ውስጥ የሚስተዋሉትን የትኛውንም ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችና ጫናዎች ለማስቀረት በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ እና ውጤትም እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et