በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው ዓመታዊ የአፈፃፀም ግምገማ ፕሮግራም የዛሬ ውሎ የዩኒቨርሲቲው የ2017 ዓ.ም መሪ ዕቅድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ የተጠናቀቀው በጀት አመት አጠቃላይ አፈጻጸም በጥልቀት በተገመገመበት ወቅት የተገኙ ውጤቶችን በማገናዘብ የተዘጋጀው የአዲሱ አመት መሪ ዕቅድ የዩኒቨርሲቲውን ራዕይና ተልዕኮ በተሻለ ደረጃ ለመፈጸም እንዲያስችል መሆኑን ገልጸዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም በ2017 ዓ.ም በትኩረት ከሚሰራባቸው ስራዎች መካከል ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር በተጀመረው ስራ ላይ የሚገጥሙንን እድሎችና ፈተናዎች በአግባቡ አጥንቶ በመለየት በቀጣይ ዓመት ወደ ሁሉም ኮሌጆች ለሽግግሩ ስኬታማነት የየድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀት ይገባቸዋል ብለዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕላንና ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ቡርቃ መሪ ዕቅዱን ለመድረኩ ተሳታፊ ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት ዕቅድ ማለት ተቋም የሚመራበት የተግባር መመሪያ እንደመሆኑ የአመቱ መሪ እቅድ የዩኒቨርሲቲውን የመካከለኛ ዘመን እቅድና የትምህርት ሚኒስቴርን አቅጣጫ አካቶ የ2016 ዓ.ም አፈጻጸምን መነሻ አድርጎ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ዕቅዱ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲ አቀፍ ግቦችንና የውጤት አመላካቾችን በማስቀመጥ የተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የአገልግሎት አሰጣጥና የመማር ማስተማር ስራውን ለማዘመን ዲጂታላይዜሽንን እንደ ዋነኛ መስፈርት ያጠቃለለ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አለሙ ጣሚሶ በኮሌጁ ተሰርተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ አዳዲስ የህክምና ማዕከላትን ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ሲያስጎበኙ የካንሰር ጨረራ ህክምና ማዕከሉ ከሪፈራሉ ተነጥሎ ለብቻው በመገንባት በሀገር ደረጃ ብቸኛ መሆኑንና በኢትዮጵያ የጨረር ህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል አራተኛው መሆኑን ተናግረዋል።