ሀዩ ለ25ኛ ዙር ተማሪዎቹን በደማቅ ስነ ሥርዓት አስመረቀ

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለ25ኛ ዙር ተማሪዎቹን በደማቅ ስነ ሥርዓት አስመረቀ::

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሁሉም ኮሌጆች የተውጣጡ 3,024 የመጀመሪያ ዲግሪ: 1,211 የማስተርስ: 38 የህክምና ስፔሻልቲ: 46 የዶክትሬት ዲግሪ እና 481 ልዩ ልዩ የመምህራን ስልጠና የወሰዱ በአጠቃላይ 4,800 (26% ሴቶች) ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት በዋናው ግቢ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በድምቀት አስመርቋል::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ባደረጉት የደስታ መግለጫ ንግግራቸው እንደገለጹት የዘንድሮውን የምረቃ በዓል ለየት ከሚያደርጉት ሁነቶች መካከል ላለፉት አራት አመታት ተዛብቶ የቆየውን የትምህርት የጊዜ ሰሌዳ ለማስተካከል በከፍተኛ ጫና ውስጥ ታልፎ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑ ነው። ለዩኒቨርሲቲው ስኬታማ ጉዞ በየደረጃው ያሉ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አካላት ላደረጉት ርብርብና ላሳዩት ትጋትና ቁርጠኝነት ፕሬዚደንቱ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል:: የዛሬ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሀገራቸውን ከማገልገል ባለፈ ራሳቸውን የሀገር አንድነት ከሚሸረሽሩት ፅንፈኝነት: ጥላቻና አድሎአዊነት እንዲያርቁ ዶ/ር አያኖ አደራ ብለዋል::

የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በበኩላቸው ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ዕለቱ የአመታት ትዕግስት፣ ጥናትና ልፋት የሚጠይቀውን ረዥሙን የትምህርት ጉዞ በቤተሰቦቻችሁ እና በዩኒቨርሲቲያችሁ እንዲሁም ደግሞ በራሳችሁ እልህ አስጨራሽ ጥረት በድል አጠናቃችሁ የራሳችሁን፣ የማህበረሰባችሁንና በአጠቃላይ የሀገራችሁን ብሩህ መጻዒ እድል ለመወሰን ትበቁ ዘንድ ወደ አዲስ የህይወት ምዕራፍ የምትሸጋገሩበት ወሳኝ ቀን በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

በዕለቱ ከነበሩ ልዩ ሁነቶች መካከል በፒ.ኤች.ዲ ፕሮግራም የተመረቁት ዶ/ር ዳንኤል ወ/ሚካኤል እና ዶ/ር ህብረት ደምሴ የተባሉ ጥንዶች በዩኒቨርሲቲው የነበራቸው ቆይታ አስደሳች እንደነበርና በአንድ ላይ መመረቃቸውም ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ሌላኛዋ ከሎጅስቲክስ ትምህርት ክፍል 4.0 ነጥብ አምጥታ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ተመራቂ ቤተልሔም ተስፋዬ በበኩሏ በብዙ አመታት ውስጥ በጥንካሬና ተስፋ ባለመቁረጥ የተለፋው ልፋት በውጤት በመጠናቀቁ መደሰቷን ገልጻ ለሁሉም የዕለቱ ተመራቂዎች እንኳን አደረሳችሁ ብላለች።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et