በቦሪቻ የመስክ ጉብኝት ተከናወነ

በቦሪቻ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የተሻሻለ የቡና ችግኝ የመስክ ጉብኝትና ተከላ ተከናወነ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ድጋፍ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በቦሪቻ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የተሻሻለ የቡና ችግኝ የመስክ ጉብኝትና ተከላ መርሐግብር ተካሂዷል።

የክልሉ መንግስት ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የቦሪቻ ወረዳ አርሶአደሮች የታደሙበትና ባለፉት ሁለት አመታት ሲተገበር የነበረውን የቡና ችግኝ ልማት ያለበትን ደረጃ ለመመልከት እንዲሁም የዘንድሮን ችግኝ ተከላ የማስጀመር በተሰናዳው የመስክ ምልከታ ላይ ብዙ ተስፋ ሰጭ ውጤት መገኘቱ ተገልጽዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ም/ቴ/ሽ/ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ በመርሃግብሩ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎቱን በስድስት የተለያዩ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ካለፈው አመት ጀምሮ በቦሪቻና ሸበዲኖ ወረዳዎች 25,600 የሚጠጉ የተሻሻለ ዝርያ የቡና ችግኞችን በማፍላት 76 ለሚደርሱ አርሶአደሮች ከበቂ ስልጠና ጋር ማቅረቡንና በኩታ ገጠም በተሰራው ስራ በአርሶአደሩ ማሳ ላይ አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ቡና ፍራፍሬና ቅመማቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው በሲዳማ ክልል የሚገኙና በባህርዛፍ የተሸፈኑ ማሳዎችን በቡናና ሌሎች ፍራፍሬዎች የመተካት እቅድ በክልል ደረጃ መያዙንና ተፈጻሚነቱን ለማሳለጥ ህግ ሆኖ ጸድቆ በቀጣይ ሶስት አመታት እውን ለማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል። ይህን ውጥን በተያዘው እቅድ መሰረት ለመፈጸም ከአርሶአደሩ ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉና ከአየር ንብረቱ ጋር ተስማሚ የሆኑ የቡና ችግኞችን በማቅረብ ከወረዳ ጽ/ቤቶች ጋር እያደረገ ለሚገኘው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የቦርቻ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በየነ ሐሪሶ ወረዳውና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቡና ልማት ላይ በጋራ መስራት ከጀመሩ ሁለት አመታት መቆጠሩንና በዚህ ጊዜ ውስጥ 3.5 ሔክታር ኩታ ገጠም መሬት ላይ የቡና ችግሮች መተከላቸውን እንዲሁም ተጨማሪ 4 ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎቱ በኩል በየጊዜው ያልተቋረጠ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የቡና ምርቱን ደረጃ እንደሚገመግምና መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች ላይ በጋራ በመነጋገር ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝ የገለጹት አስተዳዳሪው ከዚህም ስራ አርሶአደሩ ከፍተኛ ተጠቃሚ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በሀ/ዩ ግብርና ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ደረጄ ኃይሌ ባህርዛፍ በመሬት ለምነትና በዙሪያው ለሚገኙ ተክሎች ተጽዕኖ እንደሚያመጣ በመጠናቱ ይህንኑ ሀሳብ ለአርሶአደሩ በአግባቡ በማስረዳት ባህርዛፍን በመንቀል ውጤታማ የሚያደርጉ የቡናና ሌሎች የፍራፍሬ ዝርያዎችን በኩታ ገጠም ማሳዎች እንዲተክሉ ስራ መሰራቱን ገልጸው ይኸው ስራ በጥሩ ውጤት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለትም በዩኒቨርሲቲው የቡና ማፍያ ጣቢያ የተዘጋጁ ከ7,000 የሚበልጡ ችግኞችን ለማበርከትና ከአንድ አመት በፊት የተተከሉ የቡና ችግኞች ያሉበትን ደረጃ ለመመልከት መርሐግብሩ መሰናዳቱን የጠቆሙት ዶ/ር ደረጄ በአርሶአደሩ በኩል እየታየ ያለው መነሳሳት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et