ከሲዳማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጋር የመግባብያ ስምምነት ተፈረመ

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጋር የመግባብያ ስምምነት ተፈራረመ::

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጋር በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ላይ በቅንጅት ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ውል ሰኔ 11/2016 ዓም ተፈራረመ::

በፊርማው ስነስርዓት ላይ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊትም ከቢሮው ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው አሁን የመግባቢያ ውል መፈራረሙ የቀሩትን ሥራዎች በብቃት ለማጠናቀቅ ያስችለናል ብለዋል:: በክልሉ የትምህርት ጥራት ማሻሻያና የአፈር አሲዳማነት መከላከያ ላይ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በራሱ ወጪ ጭምር ጥናቶችን እየሰራ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አሰራር እንዲሰፍን የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነም ፕሬዚደንቱ ጠቁመው እስካሁን ብዙ ቢሮዎችን በእውቀት እየደገፍን እንደሆነው ሁሉ ወደፊትም አስፈላጊ በሆነበት ሁሉ ድጋፋችንን እንቀጥላለን ብለዋል::

የምርምርና ቴክ/ሽ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በበኩላቸው የክልል ቢሮዎች ስራቸውን በእውቀትና በምርምር የተገኘ መረጃ ላይ ተመርኩዘው ለመስራት ማሰባቸው እጅግ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው ነገር ግን የጥናት ውጤቶች ወደ ተግባራዊ ሥራ ካልተቀየሩ ማስጠናት ብቻውን ግብ አለመሆኑን አሳስበዋል::

የሲዳማ ብ/ክ/መ/ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ መንግስት የተለያዩ ቢሮዎች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አመስግነው ዩኒቨርሲቲው ለክልሉ ህዝብ የሚያደርገውን ዘርፈብዙ አስተዋፅኦ በኢንዱስትሪው ረገድም መጨመሩ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ አስምረውበታል:: ከዚህ ቀደም የኢንዱስትሪ ፍኖተ ካርታ (industry road map) እና ስትራቴጂክ ዕቅድ አብረን እንደመስራታችን በቀጣይነት ደግሞ ጥናቱን ሰርቶ ሰነድ ከማስቀመጥ ባሻገር በተግባር ሥራ ላይ ለማዋል እና ለአምራች ኢንዱስትሪ ሥራ ማስተዋወቂያና በመረጃ ላይ የተመሰረተ አቅጣጫ ለመስጠት: ተበታትነው ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የማሰባሰብ ሥራ ላይ ዩኒቨርሲቲው እንዲሰራ መፈለጋቸውን ኃላፊው አክለዋል::

የመግባቢያ ስምምነቱን ተከትሎ በአንድ ዓመት ውስጥ ተሰርቶ የሚጠናቀቀውን የማማከርና የምርምር አገልግሎት ሥራ ምክረሃሳብ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ኢ/ር ፋሲካ ቤተ: ዶ/ር ፈንታሁን ሞገስ እና አቶ አለማየሁ ተስፋዬ የዕቅዱን ይዘትና ዓላማ: ዝርዝር ቴክኒካል ዕቅድ እና የፋይናንስ ዕቅድ ዝርዝር ምክረሃሳብ በመድረኩ አቅርበዋል::

በመጨረሻም የሀ/ዩ/ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ እና የሲ/ብ/ክ/መ/ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና የሁለቱም ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ስምምነቱን ተፈራርመዋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et