ለተደራጁ የወጣት ማህበራት ድጋፍ ተደረገ

ሀዩ በሲዳማ ክልል መልጋ ወረዳ ለተደራጁ የወጣት ማህበራት የተሻሻለ ዝርያ የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት ድጋፍ አደረገ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በሲዳማ ክልል መልጋ ወረዳ ለተደራጁ የወጣት ማህበራት 1,200 የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶች አቅርቦ ያስጀመረውን ሥራ ያለበትን ሁኔታ ለባለድርሻ አካላት አስጎበኘ::

ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ መንደሮች አንዱ በሆነው መልጋ ወረዳ ወጅግራ ከተማ ያለውን የተቀናጀ የዶሮ እርባታ ስራ ለባለድርሻ አካላት ለማስጎብኘት ዛሬ በተካሄደው የመስክ ውይይት የወረዳውና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የመልጋ ወረዳ አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ሳሙኤል ኩሌሎ ወረዳው በአንድ ኢንተርፕራይዝ አምስት ወጣቶችን ካደራጀ በኃላ የሀዩ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ስልጠና በመስጠት: የአንድ ቀን ጫጩቶችን ለአርባ ቀናት አርብተው ለህብረተሰቡ ገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ማህበራቱን ወደስራ ማስገባቱን ገልጸው የዶሮ ጫጩትና የመኖ ድጋፍ እንዲሁም ያልተቋረጠ ሙያዊ ድግፍ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መስራቱን አመስግነዋል:: ከዚህ በፊት ተሞክሮ ያልተቻለውን በማስቻሉ ዩኒቨርሲቲው ትልቅ የስኬት መንገድ እንዳሳየ የገለፁት አስተዳዳሪው በቀጣይነትም በትብብር የመስራት ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ሲሰራ እንደቆየ ገልፀው በራሱ የግብርና ኮሌጅ በኩል የተፈለፈሉትን የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የአንድ ቀን ጫጩቶች ለተለያዩ ማህበራት የሚያደርገው ድጋፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉም ባለድርሻ አስተዋፅኦ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል:: "እኛ የምንሰጠው የመነሻ ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው የማስፋፊያ ሥራውን ከክልሉ እና ከወጣቶች ይጠበቃል እንጂ ወጪና ገቢውን በእውቀት እያስተዳደሩ መቀጠል ካልቻሉ ውጤት አይኖርም" ያሉት ዶ/ር አያኖ ለስራ አጥ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲው ያለውን አቅም በአግባቡ ተጠቅሞ የአንድ ቀን ጫጩት ማቅረብ ላይ ለክልሉ ጭምር ለማድረስ ጠንክሮ ይሰራል ብለዋል::

የምርምርና ቴክ/ሽ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በበኩላቸው ሀዩ በተመረጡ ጭብጥ ተኮር ዘርፎች ማለትም በሰብል ልማት፣ እንስሳት እርባታ፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ትምህርት እና ስነ-ምግብ ዘርፎች በርካታ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በወረዳው የሚገኙ ወጣቶች በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተደራጅተው ለመስራት ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ በወረዳው የስራ እድል ፈጠራ ቢሮ የአንድ ቀን ጫጩትና የዶሮ መኖ ድጋፍ እንድናደርግ በቀረበልን ጥያቄ መሰረት ሙያዊ ስልጠና ጨምረን ድጋፍ በማድረጋችን የአካባቢውን አየር ንብረት መቋቋም የሚችሉ 1,200 የዶሮ ዝርያ ጫጩቶችን በራሳችን ባለሙያዎችና መፈልፈያ ማሽን አምርተን ለውጤት በቅተናል ብለዋል።

የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ም/ኃላፊ ዶ/ር አደገ አየለ የዶሮ እርባታ ዘርፉ በርካታ ወጣቶችን በአንድ ጊዜ በማሳተፍ የስራ እድል ፈጠራን የሚጨምር ከመሆኑ ባሻገር የህብረተሰቡን የአመጋገብ ሁኔታ ከማሻሻል አንጻር ውጤታማ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል። ቢሮው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና በወረዳዎች መካከል እየተደረገ ያለው ጠንካራ የትብብር ስራ እንደ ሀገር ትኩረት የተሰጠው የሌማት ትሩፋት ዕቅድን ለማሳካት የሚያስችል ሰፊ ዕድል እየፈጠረ እንዳለ ይገነዘባል ሲሉ ኃላፊው አክለዋል።

በማህበር የተደራጁት ወጣቶች ስለተደረገላቸው ከፍተኛ ድጋፍ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያመሰገኑ ሲሆን በስራቸው ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች አንስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል:: በውይይቱ ማጠቃለያ በብዛት እንደ ከባድ ተግዳሮት የሚነሳው የዶሮ መኖ ጥያቄ የሚመለስበትን መንገድ እንደሀገር እና እንደምርምር ተቋም ጠንክረን መፍትሄ ልናበጅለት ይገባል ሲሉ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ለሁሉም ባለድርሻ አሳስበዋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et